ክርስቲያኖ ሮናልዶ የፖርቱጋል “ታላቁ ምልክት” ነው — ብሩኖ ፈርናንዴስ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ የፖርቱጋል “ታላቁ ምልክት” ነው — ብሩኖ ፈርናንዴስ



አዲሱ የፖርቱጋል ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ጆርጄ ጄሰስ ከዴንማርክ ጋር በተደረገው የኔሽንስ ሊግ ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በቋሚ ተሰላፊነት እንደማይጀምር በመንገራቸው ምክንያት የ41 ዓመቱ አጥቂ ሮናልዶ የቡድኑን ካምፕ ለቆ መውጣቱ ይታወሳል።



ይህንን ተከትሎም ለፖርቱጋል ብሔራዊ ቡድን በ234 ጨዋታዎች 146 ግቦችን በማስቆጠር የምንግዜም ጊዜ ከፍተኛ ግብ አግቢ የሆነው እና የዩሮ 2016ን ዋንጫን ያነሳው ሮናልዶ፣ ከአገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያለው የወደፊት ቆይታ አሁን ላይ አጠራጣሪ መሆኑ ተነግሯል።



ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የማንችስተር ዩናይትዱ አማካይ ብሩኖ ፈርናንዴስ በሰጠው አስተያየት “ከክርስቲያኖ ጋር ተነጋግሬአለሁ፤ የነገርኩት እና እዚህም የምደጋግመው ነገር ቢኖር፣ ምንም ይፈጠር ምን ክርስቲያኖ ሮናልዶ በፖርቱጋል ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ላከናወነው ነገር የብሔራዊ ቡድናችን፣ የእግር ኳሳችን እና የአገራችን ታላቁ ምልክት ሆኖ ይኖራል” ብሏል።



ፈርናንዴስ አያይዞም በሕዝቡ እና በደጋፊዎች መካከል መከፋፈል ሊፈጠር እንደማይገባ አፅንዖት ሰጥቶ ተናግሯል።



“እሱ በታሪክ ከታላላቆቹ እኩል ብቻ ሳይሆን በሁሉም ፖርቹጋላውያን ልብ ውስጥ የተለየ ቦታ አለው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ነገሮችን መከፋፈል ማቆም አለብን። ከውጭ በሚመጡ ድምጾች ሳቢያ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ምንም አይነት ክፍፍል የለም፤ ወደፊትም አይኖርም” ሲል አክሎ ገልጿል።



አሰልጣኝ ጆርጄ ጄሰስ በበኩላቸው ሮናልዶ የፖርቱጋል “ምልክት” መሆኑን ገልጸው፣ ስለ እርሱ ሁኔታ ከኖርዌይ ጋር ከሚደረገው ጨዋታ በኋላ ሰፊ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።



በአሰልጣኝ ጆርጄ ጄሰስ የሚመራው የፖርቱጋል ብሔራዊ ቡድን በኔሽንስ ሊግ ምድብ A4 በሶስት ጨዋታዎች ሙሉ 9 ነጥብ ሰብስቦ መሪነቱን ይዟል።



ፖርቱጋል ዛሬ ምሽት 3 ከ45 ላይ ከኖርዌይ ጋር በሜዳዋ የምድቧን 4ኛ ዙር ጨዋታውን ታከናውናለች።



ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ