መስቀል የድህነት ምልክት መሆኑን የካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ አህጉረ-ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ህዝቅኤል ተናገሩ

መስቀል የድህነት ምልክት መሆኑን የካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ አህጉረ-ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ህዝቅኤል ተናገሩ

መስቀል በመከራና በስደት ውስጥ የተገኘ የድህነት ምልክት እንደሆነ የካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ አህጉረ-ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ህዝቅኤል ተናገሩ።

የመስቀል ደመራ በዓል በቦንጋ ከተማ ሲከበር ባስተላለፉት መልዕክት፤ የጌታ መስቀል ለብዙዎች የድህነት ምልክት መሆኑንና የሰው ልጅ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ የወጣበትና ጸጋችን የተመለሠበት መሆኑን ተናግረዋል።

የመስቀል በዓል ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ዓለምን ማዳኑን፣ መስቀል በክርስቶስ ደም የከበረ መሆኑን በመግለጽ፤ ለሰው ልጆች መዳን ሲል ፍቅሩን የገለጸበት የርህራሄ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው እለት የድህነታችን ምልክት የሆነውን የመስቀል ደመራ በዓል እያከበርን እንገኛለን ያሉት ብፁዕ አቡነ ህዝቅኤል፤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የቦንጋ ከተማ ከንቲባ ተክልአብ ቡሎ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆኑት የአብሮነት፣ የመደጋገፍ፣ የእርቅና መሰል እሴቶች ደምቀው የሚንጸባረቁበት በዓል እንደመሆኑ ይህንን በዓል በአብሮነት፣ በመተሳሰብና በመጠያየቅ ማክበር ይገባል ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት አንዱ መሆኑን እና በዓለም-አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ እንዲሁም ትኩረት የሳበ በዓል ነው ብለዋል።

ደመራው የጨለማችን ማብቂያ መስቀሉ አንድነታችን ይሁን በማለት
ለመላው ህዝበ-ክርስቲያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ፈጠነ ወንድሙ – ከቦንጋ ጣቢያችን