የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነዉ “ያሆዴ” ከየትኛውም ሃይማኖታዊ ስርዓት ጋር የማይጋጭ የብሔሩ ቱባ ባህላዊ እሴት መሆኑ ተገለጸ

የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነዉ “ያሆዴ” ከየትኛውም ሃይማኖታዊ ስርዓት ጋር የማይጋጭ የብሔሩ ቱባ ባህላዊ እሴት መሆኑ ተገለጸ

የ”ያሆዴ” በዓል በሆሳዕና ከተማ ደረጃ የማጠቃለያ ፕሮግራም በኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ አደባባይ ተከብሯል።

በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር በኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ በከተማ ደረጃ በተከበረው “ያሆዴ” ለሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትንሣኤ ታደሰ እንዳሉት፤ በዓሉ በከተማ ደረጃ ለአንድ ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶ ሲከበር መቆየቱን ተናግረዋል።

በከተማ ደረጃ የማጠቃለያ ስነ-ስርዓቱ በደማቅ ሁኔታ መከበሩን የገለጹት ኃላፊው መስከረም 12 እንደ ዞን በሀድይ ነፈራ የሚከበረውን በዓል ለማክበር ከሀገር ውስጥና ከውጪ የሚመጡ እንግዶችን ለማቀበል ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ በበኩላቸው፤ የዘንድሮ “ያሆዴ” በዓል በከተማዋ በርካታ ክልላዊና አገራዊ ሁነቶች በተስተናገዱበት ማግስት መሆኑን ጠቁመው በዓሉም የአንድነት፣ የመቻቻል፣ የይቅርታ እና የዕርቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

የ”ያሆዴ” በዓል ከማንኛውም ሃይማኖት ጋር የማይጋጭ የብሔሩ ቱባ ባህላዊ እሴት መሆኑን የገለጹት ከንቲባዉ፤ በዓሉን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (በዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን ማበርከት እንደሚገባውም አሳስበዋል።

የሀዲያ ዞን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ በዕለቱ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት፤ የዘንድሮ የ”ያሆዴ” በዓል ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተው አይግባቡም የተባለውን ሀሳብ ቀይረው በሀገር ጉዳይ መክረው በተግባቡበት ማግስት የሚከበር መሆኑ የበዓሉን ደስታ ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

“ያሆዴ” የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ እና ከመቼም በላይ ፍቅራችን የሚጎለብትበት በዓል መሆኑን ህብረተሰቡ በመገንዘብና ከየትኛውም ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ጋር የማይጋጭ በመሆኑ መስከረም 12 በዞን ደረጃ በሀዲይ ነፈራ በሚከበረው በዓል ላይ ሁሉም የከተማው ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተዉ እንዲታደሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በበዓሉ የተሳተፉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው “ያሆዴ” የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(በዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የተጀመረው እንቅስቃሴ ከዳር እንዲደርስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል።

ለበዓሉ ታደሚዎችም በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀው የከተማውን ማህበራዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ገፅታ የሚያሳዩ
የፎቶ አውደ ርዕይና ኤግዚቢሽን በከተማው መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ በሆኑት በአቶ ኃ/እግዚአብሔር ለምጃቦ አማካኝነት ገለፃ ተደርጓል።

በበዓሉ ላይም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የመጡ ከንቲባዎች፣ የከተማዋና የዙሪያዉ ነዋሪዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን