“ከማክስ ዶውማን ጋር መስራት ትልቅ ደስታ ነው” ሚኬል አርቴታ
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ዋና አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የ16 ዓመቱን ድንቅ ታዳጊ ማክስ ዶውማንን ማሰልጠን “ትልቅ ደስታ” እንደሆነው ገልፀዋል።
ታዳጊው ተጫዋች ትናንት ምሽት በካራባኦ ካፕ ከኢፕስዊች ጋር በተደረገው ጨዋታ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር አርሰናል 4 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸናፊ እንዲሆን የራሱን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ማክስ ዶውማን በፕሪሚየር ሊግ ክለብ ታሪክ ከዋይን ሩኒ (እ.ኤ.አ በ2002 ከኤቨርተን ጋር) በመቀጠል በአንድ ጨዋታ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረ ሁለተኛው የ16 ዓመት ታዳጊ በመሆን ስሙን በታሪክ አስመዝግቧል።
አርቴታ ስለ ተጫዋቹ ሲናገሩ“ከእሱ ጋር መስራት ትልቅ ደስታ ነው። ግቦችን ሲያስቆጥር እና ድንቅ ዕድሎችን ሲፈጥር ስለሱ ማውራት የማይቀር ነው። ትልቁ ጥንካሬው እነዚህን ድርጊቶች ያለ ድካም መፈጸሙ ነው“ ብለዋል።
አሰልጣኙ አያይዘውም በዋናው ሊግ ውስጥ በዚህ የዕድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ታዳጊዎች ማሰለፍ እና አካላዊ ጥንካሬያቸውን መቋቋም እጅግ ከባድ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ ይሁን እንጂ ዶውማን ይህንን ፈተና በብቃት እየተወጣው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በታዳጊው ዙሪያ የሚፈጠረውን ከፍተኛ የሚዲያ ጫና እና ውዳሴ መቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑን አርቴታ ቢቀበልም፣ ክለቡ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ተጫዋቹን በአግባቡ በመንከባከብና በትክክለኛው መንገድ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
“በአውሮፓ ሌሎች ሊጎች ይህ የተለመደ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በእኛ ሊግ ውስጥ ያለው ከባድ ጫና እና ፍላጎት የተለየ ነው። እያንዳንዱን እርምጃ ስንወስድ በትክክለኛው ዝግጅት መሆን አለበት“ ሲሉ አርቴታ አክለው ገልፀዋል።
ይህ ድንቅ ታዳጊ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳየው የአእምሮ ብስለት እና በትልቅ የውድድር መድረክ የመጫወት ፍላጎት አርሰናልን ለወደፊት ስኬቶች እንደሚያበቃው ተስፋ ተጥሎበታል።
ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ስፖርት ፍቅርን፣ ሰላምን እና አንድነትን ለማምጣት ወሳኝ ነው – የቡርጂ ዞን አስተዳደር
“እናቴ ሆይ ደውይልኝ!”
የአባቱ ልጅ!