በመስኖ አምርተው የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ

በመስኖ አምርተው የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ

መንግስት የአርሶአደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የጎፋ ዞን በቶ ከተማ አስተዳደር ግብርና ዩኒት አስታወቀ።

አርሶ አደሩ ከባህላዊ አስተራረስና ከወቅት ጠባቂነት ተላቆ በዘመናዊ አስተራረስ እንዲያመርት በመስኖ ፕሮጀክት ከታቀፉ አራቱ ቀጠናዎች ሶስቱ ተደራሽ በመሆናቸው ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን የበቶ ከተማ አስተዳደር ግብርና ዩኒት መሪ አቶ ቡራቃ ቡጫራ ገልፀዋል።

አርሶ አደሩ በሙሉ ፓኬጅ በመዝራትና የተሻለ ምርት በማምረት ከኢሊኖ ተፅዕኖ ነፃ መሆናቸውን አንስተው፤ የመንግስት ትኩረት የአርሶአደሩ የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ በመሆኑ በተሰራው ሥራ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።

አስተያየት ከሰጡን ተጠቃሚ አርሶ አደሮች መካከል አርሶአደር ባደና ባርዳ እና ደበበ ደልኮ እንዳሉት፤ ከዚህ በፊት መስኖን በባህላዊ መንገድ ሲጠቀሙ ይቸገሩ እንደነበር አንስተው፤ መንግስት በዘመናዊ መንገድ ካመቻቸላቸው በኋላ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ ቲማትም እና የሰብል ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ሞደል አርሶአደር ብዙነሽ ሽሎቴ በአንፃሩ የመስኖ ስራውን በጄነሬተር በሚሰራ ፓምፕ ሲጠቀሙ በመቆየታቸው የነዳጅ ወጪ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘመናዊ መስኖን በመጠቀም ስንዴ፣ ቃሪያ፣ ሽንኩርት እና ቲማትም በማምረት በወር ከ120 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙ ለ3 ሰዎች የስራ ዕድል በመፍጠራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወይዘሮ አማረች ካሎሴ እና ወጣት አቤል አብርሃም እንዳሉት፤ ተቀጥረው እየሰሩ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን በማንሳት በቀጣይ በግል የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ ኢያሱ አዲሱ – ከሳውላ ጣቢያችን