ስፖርት ፍቅርን፣ ሰላምን እና አንድነትን ለማምጣት ወሳኝ ነው – የቡርጂ ዞን አስተዳደር
ስፖርት ፍቅርን፣ ሰላምን እና አንድነትን ለማምጣት ወሳኝ ነው ሲሉ የቡርጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትንሳኤ ዮሐንስ ተናገሩ፡፡
በዞኑ በክረምት ወራት በ18 ዘርፎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ላለፉት ሁለት ወራት ሲካሄድ የቆየው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆነው የእግር ኳስ ውድድር ፍፃሜውን አግኝቷል።
በማጠቃለያ መርሃግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቡርጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትንሳኤ ዮሐንስ እንደተናገሩት፤ ስፖርት ፍቅርን፣ ሰላምን እና አንድነትን ለማምጣት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ውድድሩ ብዙ ተስፈኛ ተተኪ ስፖርተኞች የታዩበት ነው ያሉት አስተዳዳሪው፥ ክልሉንም ሆነ ሀገርን ወክለው መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾች በእንደዚህ ዓይነት መድረኮች እንደሚገኙ አንስተዋል።
በቡርጂ ዞን ባህል እና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ውድድር ቡድን መሪ አቶ ቦሮ አዶ በበኩላቸው፤ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል በሆነው እግር ኳስ ውድድር 29 ቡድኖች መሳተፋቸውን ጠቅሰው ከእነዚህ ውስጥ 12 የአዋቂዎች እና 17 ታዳጊ ቡድኖች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በስፖርቱ የተሳተፉ አካላት በሰጡት አስተያየት የውድድሩ መዘጋጀት ወጣቶች አልባሌ ቦታ ከመዋል በማላቀቅ በአካልም ሆነ በአእምሮ ንቁ ሆነን እንድናሳልፍ አግዞናል ሲሉ ውድድሩን ላዘጋጁ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በታዳጊዎች ፍፃሜ ‹‹ሀሳና›› እና ‹‹ወረደያ›› የተገናኙ ሲሆን ጨዋታውን ሀሳና 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡
በአዋቂዎች ‹‹ዶልቻ›› እና ‹‹ክሊኒክ›› እግር ኳስ ቡድኖች ተገናኝተው ክሊኒክ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።
ዘጋቢ፡ ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
“ከማክስ ዶውማን ጋር መስራት ትልቅ ደስታ ነው” ሚኬል አርቴታ
“እናቴ ሆይ ደውይልኝ!”
የአባቱ ልጅ!