በፍትሕ ዘርፍ የሚታየው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ አስታወቁ

በፍትሕ ዘርፍ የሚታየው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ አስታወቁ

የጉራጌ ዞን ፍትሕ መምሪያ “ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል፣ በ2018 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸምና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የሚመክር የሴክተር ጉበኤውን በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ በዚሁ ጊዜ እንዳስታወቁት፤ ፍትሕ ያለምንም አድልዎና መገለል ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ መሆን አለበት።

የፍትሕ አገልግሎቱ በሕዝቡ ዘንድ ተዓማኒና ተቀባይነት እንዲኖረው፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ከሙስናና አድልዎ የጸዱ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

አቶ ደሳለኝ አክለውም፤ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የፍትሕ ዘርፉን ለማጠናከር ያላቸው ሚና የጎላ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በዞኑ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ሰብለጋ በበኩላቸው፤ መምሪያው በዞኑ ውስጥ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ከፍ ለማድረግና ቀጣይነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

ኃላፊው የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ በበጀት ዓመቱ ከፖሊስ የቀረቡ መዛግብት 1 ሺህ 125 ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ 301 በእርቅ ያለቁ፣ 25 አያስከስስም ተብሎ በዐቃቤ ሕግ የተዘጉ እና 828 መዝገቦች ደግሞ በፍርድ ቤት ክርክር የተደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰው ተከሳሽና ምስክር ባለመቅረብ የተቋረጡት ደግሞ 27 ናቸው።

በሌላ በኩል በፍርድ ቤት ውሳኔ ካገኙት 774 መዛግብት መካከል፤ 699ኙ ጥፋተኛ የተባሉ፣ 12ቱ በነፃ የተሰናበቱ ሲሆን፤ 54 መዛግብት ደግሞ ለሚቀጥለው በጀት ዓመት በቀጠሮ ተሸጋግረዋል።

የተመዘበሩ የሕዝብና የመንግሥት ሀብቶችን ከማስመለስ አንጻርም በፍትሐ-ብሔር፣ በሙስና፣ በታክስና ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች በድምሩ 58 ሚሊዮን 850 ሺህ 399 ብር እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የከተማና የገጠር መሬቶችን ማስመለስ መቻሉን አብራርተዋል።

ልዩ ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም የገቢ ኮንትሮባንድ፣ በመሠረተ-ልማት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውንም አመላክተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፣ የፍትሕ አሰጣጥ አገልግሎቱ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዞኑ ውስጥ እየተፈጸሙ የሚገኙና የኅብረተሰቡን ባህልና እሴት የማይመጥኑ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ የራሳቸውን ሚና እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መዋቅሮች ዕውቅናና ሽልማት የመስጠት እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን ከታችኛው መዋቅር ጋር የመፈራረም መርሐ-ግብር ተካሂዷል።

ዘጋቢ፡ ፍስሃ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን