የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነውን የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህል ይበልጥ በማጎልበት ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ማገዝ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታወቀ
ቢሮው “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቀቤና ልዩ ወረዳ ፈቃዶ ቀበሌ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን የአንዲት አቅመ ደካማ እናት ቤት ርክክብ መርሐ-ግብር አከናውኗል።
የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ከቅን ልብና ከመልካም አስተሳሰብ የሚመነጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በሁሉም አካባቢዎች የአቅመ ደካሞችን ቤቶች እየገነቡ መሆኑን ያነሱት አቶ ሙስጠፋ ቢሯቸውም በነሐሴ ወር ግንባታውን የጀመረውን ይህንኑ መኖሪያ ቤት አጠናቆ ማስረከቡን ገልጸዋል።
ቤቱ ደረጃውን የጠበቀ፣ የቤት ቁሳቁስ የተሟላለት፣ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ፣ መጸዳጃ ቤትና ማብሰያ ክፍል ያካተተ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኃላፊው አክለውም ዜጎችን በዘላቂነት በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ ማቋቋም ከተረጂነት መውጫ ዋነኛው መንገድ መሆኑን አንስተው ከለውጡ ወዲህ በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ወገኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድአሚን በደዊ በበኩላቸው ቢሮው በልዩ ወረዳው በመገኘት ላከናወነው የበጎ ፈቃድ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
በልዩ ወረዳው ባሉ ሁሉም ቀበሌያት የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የአቅመ ደካሞች ቤቶች ግንባታና ጥገና እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ የምግብ እህል ድጋፍ እየተደረገ መቆየቱን ገልጸው ማኅበረሰቡ በዘርፉ እያደረገ የሚገኘውን ተሳትፎ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በልዩ ወረዳው የፈቃዶ ቀበሌ ነዋሪና የቤቱ ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ ጡበቴ ሼህ ሳሊህ በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ቀደም ሲል በፈራረሰ ቤት ውስጥ ክረምት በመጣ ቁጥር ዝናብና ብርድ እየተፈራረቀባቸው ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን የመሰለ ዘመናዊ ቤት ላስገነባላቸው አካል ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
ጎረቤታቸው የሆኑት ወ/ሮ ለምራ ሙህዲንም እናትየው ያለ ረዳት በተጎሳቆለ ቤት ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው አሁን በተደረገላቸው መልካም ተግባር እጅግ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ ከቢሮውና ከልዩ ወረዳው የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል- ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በፍትሕ ዘርፍ የሚታየው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ አስታወቁ
ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠር በቅድመ ምርመራ ስራዎች ላይ ትኩሩት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በሀላባ ዞን የቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
በመስኖ አምርተው የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ