የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓል “ማሽቃሮ” አብሮነትንና ወንድማማችነትን የሚያጎላ ነው – የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ
የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓል “ማሽቃሮ” አብሮነትንና ወንድማማችነትን የሚያጎላ በዓል ነው ሲሉ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ገለጹ።
በዓሉ ሁሉንም ወገኖች በአንድ መድረክ የሚያሰባስብ ትልቅ ባህላዊ እሴት እንደሆነም ተናግረዋል።
ዋና አስተዳዳሪው በዓሉን አስመልከተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ማሽቃሮ የማንነት መገለጫ ከመሆኑም በላይ የዘር፣ የሃይማኖትና የቀለም ልዩነት ሳይኖር ሁሉም በጋራ በአደባባይ ወጥቶ የሚያከብረው በዓል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት አቶ እንዳሻው፤ የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ መምጣቱን አመልክተዋል።
በዓሉን ዘንድሮም በልዩ ሁኔታ ለማክበር በባህል ምክር ቤቱ እና በአብይና ንዑሳን ኮሚቴዎች አማካኝነት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገ ነው ብለዋል።
ማሽቃሮን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) ለማስመዝገብ የተጀመረው ተግባራዊ መርሃ ግብር ግቡን እንዲመታ ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
አካባቢው የበለጸገ የተፈጥሮ ሀብትና ቱባ ባህሎች ባለቤት መሆኑን የገለጹት አቶ እንዳሻው፤ እነዚህን ፀጋዎች ወደ ኢኮኖሚያዊ እድል መቀየር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የዘንድሮው ማሽቃሮ በዓል መስከረም 11 እና 12 ቀን 2019 ዓ.ም በቦንጌ ሻምበቶ በተለያዩ ኩነቶች በድምቀት እንደሚከበርና የብሔሩ ተወላጆች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና አጋሮች በቦንጋ ከተማ በመገኘት በዓሉን በአብሮነት እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ዋና አስተዳዳሪው ለመላው የዞኑ ህዝቦች እንኳን ለካፈቾ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ” በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ: መቅደስ ታደሰ፣ ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
በፍትሕ ዘርፍ የሚታየው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ አስታወቁ
ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠር በቅድመ ምርመራ ስራዎች ላይ ትኩሩት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በሀላባ ዞን የቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
በመስኖ አምርተው የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ