ለከተሞች መዘመን ባለሀብቱ የሚያደርገው ተሳትፎ የጎላ ሚና አለው – የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ

ለከተሞች መዘመን ባለሀብቱ የሚያደርገው ተሳትፎ የጎላ ሚና አለው – የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ

ከተሞችን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ባለሀብቱ በግልም ሆነ በጋራ የሚያደርገው ተሳትፎ የጎላ ሚና እንዳለው የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ተናገሩ።

ዋና አስተዳዳሪው ይህንን የተናገሩት ጉራአሜ ኢንቨስትመንት አክሲዮን ማኅበር በወልቂጤ ከተማ ጉብሬ ክፍለ-ከተማ ያስገነባውን ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያ ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

የእንግዳ ማረፊያውን ሥራ በይፋ ያስጀመሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ፤ የጉራአሜ ኢንቨስትመንት ቦታ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ የጉራጌ ተወላጆች የተሰባሰቡበት በመሆኑ የቦታው ባለቤትነት ለመላው ጉራጌ የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከተወላጅ ባለሀብቶች በቂ ትኩረት ሳያገኝ መቆየቱን አንስተው፤ ከተማውን ለባለሀብቶች እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

አክለውም የጉራጌ አቅም ትልቅ በመሆኑ ከተማን ለማዘመን የተጀመረው ይህ ትልቅ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጉራአሜ ኢንቨስትመንት አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዲሱ እጥፉ ማኅበሩ አካባቢን የማልማት ዓላማ ሰንቀው በአሜሪካ በሚኖሩ ጥቂት የጉራጌ ተወላጆች መጀመሩን ገልጸዋል።

ከ15 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ይህ አክሲዮን ማኅበር፣ በውስጡ በርካታ ፕሮጀክቶችን ያካተተ ሲሆን ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ሌሎች ልማቶች ወደ ስፍራው እንዲመጡ በር መክፈቱን ሰብሳቢው አብራርተዋል።

የአክሲዮን ማኅበሩ አባላት የሆኑት አቶ ክንፈ ግርማ እና አቶ ወልዴ ዘበርጋ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት አካባቢን ለመለወጥ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመው ድርጅታቸው የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለዚህ ደረጃ መድረሱ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ነስሩ ሀሰን፣ የዞን የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር፣ የአክሲዮን ማኅበሩ አባላት እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን