በተጠናቀቀው በጀት አመት እንደሃገር ሆነ በልዩ ወረዳው ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ስኬታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉ ተገለጸ

በተጠናቀቀው በጀት አመት እንደሃገር ሆነ በልዩ ወረዳው ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ስኬታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተጠናቀቀው በጀት አመት እንደሃገር ሆነ በልዩ ወረዳው ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ስኬታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉን በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክር ቤት ገለጸ።
‎ምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 13ኛ አመት 35ኛ መደበኛ ጉባኤውን በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

‎የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ፈቱዲን ሙዘሚል በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንደገለፁት፥ እንደ ሀገር የተካሄደው የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራ በልዩ ትኩረት በመተግበሩ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አመላክተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት እንደሃገር ሆነ እንደ ልዩ ወረዳ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ስኬታማ ተግባራት ተከናውኗል ብለዋል።

‎በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በኢንቨስትመንት እንዲሁም በግብርና እና በሌሎችም ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መስራት በመቻላቸው የኤክስፖርት ምርት በማሳደግ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ማግኘት መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

‎በዲፕሎማሲው ረገድ የሀገራችንን ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፥ በበጀት ዓመቱ ለካፒታል ፕሮጀክት ልዩ ትኩረት በመስጠት ለረጅም ጊዜ ከህብረተሰቡ ይነሱ የነበሩ የልማት እና መልካም አሰተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት ያስቻሉ ሥራዎች መከወናቸውንም አብራርተዋል።

‎የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሃመድአሚን በደዊ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የ2018 ዓ/ም ስራ ዕቅድ አፈፃፀሞ ሪፖርት በልዩ ወረዳው በበጀት አመቱ ለማከናወን በተያዙ ዋና ዋና ግቦች አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል::

‎አርሶ አደሩ በአመት እስከ አራት ዙር አፈራርቆ እንዲያርስ ሁኔታዎች በማመቻቸት በተሰራው ስራ በተለይም የልዩ ወረዳው ምቹ ስነምህዳር በመጠቀም በበቆሎና በጤፍ ምርት ሞዴል ሊያደርጉ የሚችሉ ስራዎች እየተሰሩ መምጣቱ ነው የተናገሩት።

‎የልዩ ወረዳው ተወላጅና መላው የልማት ደጋፊዎችን በማሳተፍ የህዝቡ የረዥም ጊዜ ጥያቄ የነበረው ሆስፒታል ስራ ግንባታ የተጀመረበትና ለዚህም በአንድ ቀን እስከ አንድ ቢልየን ብር ቃል የተገባበት እንዲሁም የአዳሪ ት/ቤት ግንባታ ለማስጀመርም የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት አመት እንደነበርና ይህም በትልቁ ሊጠቀስ የሚችል ስኬት መሆኑ ነው ዋና አስተዳዳሪው ያብራሩት።

‎በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የመንገድ ግንባታ ስራ ዘርፍ አበረታች ተግባራት መፈፀማቸውን አመላክተው፥ የጤናውን ዘርፍ ለማዘመንና ለማሻሻል በርካታ ስራዎች መሰራቱን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፥ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋፋትም በተወሰደው እርምጃ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ እስከ 50 ሚልዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ግብአት የማሟላት ስራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል።

‎ያለፈው በጀት አመት መልካም ተሞክሮዎችን በማስቀጠል በ2019 በጀት አመት ይበልጥ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች በተለይም የተጀመሩ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ልማት ወዳዱን ህብረተሰብ በማሳተፍ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

‎የጉባኤው ተሳታፊ የምክር ቤት አባላት ያለፈው በጀት አመት የተከናወኑ ተግባራት ይበል የሚያሰኙ እንደነበር ገልፀው፥ በቀጣይ ሊሰሩ የታቀዱ ተግባራት በተገቢው እንዲተገበሩ በቅርበት እንደሚከታተሉና እንደሚደገፉም ተናግረዋል።

‎ምክር ቤቱ የልዩ ወረዳውን የ2019 በጀት ዓመት 603 ሚሊዮን 218 ሺህ 414ብር በጀት በማፅደቅ ጉባኤው ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን