ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ስራ ዓለም ሲገቡ የሚገጥሙ ችግሮችንና የስራ ጫናዎችን እንደ መሰናክል ሳይሆን እንደ እድል መጠቀም እንደሚገባው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ
የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዲግሪና ዲፕሎማ መርሃ ግብር በተለያዩ የጤና የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 መቶ 2 ተማሪዎችን አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን፤ የጤና ሳይንስ ባለሙያ መሆን ከሌሎች ሙያዎች የተለየ ኃላፊነት ያለው በመሆኑ ከመረጃ ብቻ ሳይሆን ከሰው ህይወት ጋር ጭምር ነው ብለዋል።
እናቶችን የምትደግፋ፣ አዲስ ህይወት ወደዚህ ዓለም ሲመጣ የምትቀበሉ እና ቤተሰቦችን በተስፋ የምትሞሉ ባለሙያዎች እንዲትሆኑ ሲሉም አቶ ማሙሽ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ወደ ስራ ዓለም ስትገቡ የሚገጥሙ ችግሮችንና የስራ ጫናዎችን እንደ መሰናክል ሳይሆን እንደ እድል እንዲጠቀሙም መክረዋል።
የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ኤሊያስ ቲራጎ እንደገለፁት፤ ኮሌጁ የህብረተሰቡን ጤና ለማጎልበት በሥነ-ምግባር የታነጹ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።
በኮሌጁ የምዘና ስርዓትን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ከወረቀት ነጻ በሆነ መልኩ ሠልጣኞች እንዲመዘኑ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ኤልያስ ጠቅሰዋል።
የጤናውን ዘርፍ በማዘመንና በማጠናከር ጤናማ እና አምራች ህብረተሰብ ለመፍጠር የተቀረጸውን ፖሊሲ ስኬታማ ለማድረግ ኮሌጁ በጤና ዘርፍ ችግር ፈቺ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የኮሌጁ ምክትል ዲንና የመማር ማስተማር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ድንቁ ዳንኤል በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች ላለፋት ተከታታይ አምስት ዓመታት በደረጃ-4 በዲፕሎማ እና ዲግሪ መርሃ-ግብር በጤና ኤክስቴንሽን፣ በሜዲካል ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ እና በፋርማሲ ፕሮግራሞች የሰለጠኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በዕለቱም በተለያዩ የትምህርት መስኮች በዲፕሎማና በዲግሪ መርሃግብር የሰለጠኑ 2 መቶ 2 ተማሪዎች መመረቃቸውን የገለጹት ዲኑ፤ ተመራቂዎች በመንግስትም ሆነ በማህበረሰቡ የሚሰጡ ተግባራትን በብቃት እንዲወጡ መክረዋል።
ያነጋገርናቸው አንዳንድ ተመራቂዎችም በተመረቁበት የትምህርት መስክ በቅንነት እና በታማኝነት ህዝብንና መንግስትን በትጋት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
“የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የአንድ ተቋም፣ የአንድ ፓርቲ ወይም የአንድ ትውልድ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፤ የጋራ ኃላፊነታችን ነው” – ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)
የገቢ መሠረቶችን አሟጦ በመጠቀምና በመሠብሰብ የዞኑን የገቢ አቅም ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ የጋሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ አስተዳደር ከ114 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የጤና ጣቢያ የምረቃ ስነ-ስርአት እየተካሄደ ይገኛል