የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ብቁ፣ በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ እንዲፈጠር ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት መስራት ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 23/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ብቁ፣ በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ እንዲፈጠር ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን የጉንችሬ ብራይት ቅድመ 1ኛ እና 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ብቁ፣ በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ እንዲፈጠር ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊስራ ይገባል።
ትምህርት ቤቱ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ እንዲበቃ ላደረጉ ለሚስተር ሮቤርቶ ቤተሰቦች እና ካንትሪ ዳይሬክተር ሆነው እየሰሩ ላሉ አካላት ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አክለውም ሀሳብን ወደ ተግባር በመተርጎም ፕሮጀክቱን እውን ላደረጉ ሁሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በራሳቸው እና በክልሉ መንግስት ስም ምስጋናቸውን ቸረዋል።
በኢትዮጵያ የልማት ስራ ተጀመረ እንጂ አዳጊ የሆነውን የህዝብ ፍላጎትን በማሟላት ረገድ ቀሪ ስራዎች እንዳሉ በመጠቆም በቀጣይም በዘርፉ የተጀመረው ስራ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የአካባቢው ተወላጆች ተባብረን የልጆቻችንን የወደፊት ብሩህ ተስፋ ማለምለም ይገባል ብለዋል።
የዚህ ዘመን ትውልድ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳዳሪ መሆንን ይሻል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም ዘመኑን የሚመጥን እና የሚዋጅ ስራ ይጠይቃል ሲሉ ነው የተናገሩት።
ትምህርት አለምን የሚለውጥ መሳሪያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ህጻናት ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው ማደግ እንዲችሉ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ተያይዘን ኢትዮጵያን እና ክልላችንን እንገነባለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን እናደርጋለን ሲሉም ጠቅሰዋል።
ከትምህርት ቤት ግንባታ ባለፈ በጤናውም ዘርፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል እርስቱ ይርዳው በዚሁ ጊዜ፤ መጀመሪያ መዋዕለ እጻናት መገንባት ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ነው የገለፁት፡፡
መንግስት የህዝቡን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ አስታውቀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች የህጻናት ትምህርት ቤት እንዲገነባላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ በልበ ቀናነት በመቀበል ወደ ተግባር በመገባቱ ለውጤት በቅቷል ሲሉ ገልጸዋል።
በከተማው ቅድመ 1ኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት በዛሬው እለት ለምረቃ ማብቃት መቻሉን ጠቁመዋል።
ትምህርት ቤቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ዲዛይን ከመንደፍ ጀምሮ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የቼንትሮ ኢትዮጵያ መስራች እና ፕሬዝዳንት ለነበሩት ሮቤርቶ ራባቴኒ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዛሬ እኒህ ልበ ቀና አባት በህይወት ባይኖሩም ህያው ስራቸው በትውልዱ ዘንድ ሲታወስ እንደሚኖርም አስረድተዋል።
ከነባር ይዞታቸው ተነስተው ለትምህርት ቤት ግንባታ እንዲሆን ትብብራቸውን ለገለጹ ነዋሪዎች እና ለወንድም ተስፋዬ ይገዙ ምስጋና አቅርበዋል።
የመደመር መንግስት ለህብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን እያበረከተ ይገኛል ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ ዛሬ የትምህርት እና የጤና ፕሮጀክቶችን አስመረቅን እንጂ ከዚህ በላቀ ደረጃ በሁሉም አካባቢዎች የልማት ስራዎችን ተደራሽ እየተደረገ ስለመሆኑም አብራተዋል።
በከተማም ሆነ በገጠር አካባቢዎች የህብረተሰቡን ህይወት ለማሻሻል የጋራ ትብብር እና ጥረት ይጠይቃል ሲሉም ኮሚሽነር ጀነራሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው በዞኑ የትምህርት እና የጤና መሰረተ ልማት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ውጤታማ አንደሆነ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን ላበረከቱ አካላት ዋና አስተዳዳሪው ምስጋና አቅርበዋል።
የኢፌዲሪ መስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እና የትምህርት ቤቱ ግንባታ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ይገዙ እንደገለጹት፤ በአካባቢና በሰፈር ሳንታጠር መስራት ከቻልን የህዝባችንን ህይወት መለወጥ ቀላል ነው።
በእርሳቸው አስተባባሪነት በተለያዩ አካባቢዎች 30 ትምህርት ቤቶችን ማስገንባት ችለናል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በትምህርት ዘርፍ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ድንበር የሌለው በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የቼንትሮ አዩቲ ፔርሌ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ፖውላ አሪቼ እንዳሉት ትምህርት የህጻናትን የወደፊት ህይወት የሚለውጥ መሳሪያ ነው።
ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየትም ተቋማቱ ተገንበትው ለአገልግሎት በመብቃታቸው ተደስተው ለስራው ውጤታማነት የአቅማቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ ፉአድ አብደላ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
አሊያንስ አርባ ምንጭ ኮሌጅ በድግሪ እና በዲፕሎማ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1462 ተማሪዎችን አስመረቀ
የአንድን ሀገር እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ትምህርትና ስልጠና ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ
ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ስራ ዓለም ሲገቡ የሚገጥሙ ችግሮችንና የስራ ጫናዎችን እንደ መሰናክል ሳይሆን እንደ እድል መጠቀም እንደሚገባው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ