‘ለኢሊኖ ፈተና የማይበገር እንስሳ እንፈጥራለን’ በምል መሪ ቃል በአሪ ዞን ባኮዳውላ አሪ ወረዳ የእንስሳት ጤና ማስጠበቂያ ክትባት ዘመቻና የመድሀኒት እደላ መርሃ ግብር በመካሔድ ላይ ነው
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ከVSF ጀርመኒ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የእንስሳት ክትባት መርሃግብርን የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች በይፋ አስጀምረዋል።
የክትባትና መድሀኒት እደላ ዘመቻው በይፋ በተጀመረበት በባኮ ዳውላ አሪ ወረዳ በአርክሻ ቀበሌ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳት ጤና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር እስክንድር ከድር እንደተናገሩት፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ የእንስሳት በሽታዎችን በዘመቻ መመከት የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሊደቀን ያለውን ፈተና ከመሻገር አልፎ የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና እድገት ከፍ ለማድረግ ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ታምኖ በትኩረት እየተሰራ ነው።
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሀም አታ እና የዞኑ ግምርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በበኩላቸው፤ ሰዎች ከእንስሳት ጋር ቁርኝት ያላቸው በመሆኑ በኢሊኖ ምክንያት የታየው የእርሻ ውጤት መቀነስ በእንስሳት ጤንነት እንዳይደገም ሕብረተሰቡ እንስሳትን ማስከተብና የእንስሳት መኖ አዘገጃጀትን ማዘመን ባሕሉ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
የባኮ ዳውላ አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሰረት ቦጋለ፤ በወረዳው የሚገኘው ማሕበረሰብ ከፊሉ አርብቶ አደር በመሆኑ ከፍተኛ የእንስሳት ምርት ስላለ በዚህ ወቅት እንስሳቱን ከሞትና ጉዳት ለመጠበቅ የተጀመረው የክትባት ዘመቻ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው ይህን ላስጀመሩና ድጋፍ ላደረጉ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳት ጤና ቡድን መሪ አቶ ባዩ ጥላሁን፤ የወቅቱን አየር ለውጥና ኢሊኖን ተከትሎ የሚከሰት የእንስሳት በሽታን ለመከላከል ታስቦ የተጀመረው የክትባት ዘመቻ የዳልጋ ከብቶችን በጎችና ፍየሎችን ከአባሰንጋ፣ አባጎርባና ከጎሮርሳ በሽታ የሚከላከል አራት አይነት ክትባት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው ከሰባት እስከ አስር ቀናት ሊቆይ እንደሚችል አስረድተዋል።
በዘመቻው በወረዳው ስር ያሉ አስራ ሁለት ቀበሌያት ተደራሽ እንደሚሆኑና ከመቶ ሰባ ሺህ በላይ የቀንድ ከብቶች ክትባቱን ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ያስረዱት ቡድን መሪው፤ ከክትባቱ ጎን ለጎንም የውጭና የውስጥ ጥገኛ መከላከያ መድሀኒት እደላ እየተካሔደ መሆኑንም አስረድተዋል።
እንስሳቶቻቸውን ሲያስከትቡ ያነጋገርናቸው አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች፤ በዚህ አስከፊ ወቅት እንስሳቶቻቸውን ከሞትና ጉዳት ለመጠበቅ የተጀመረው የክትባት ዘመቻ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው ይሕን ላመቻቹ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን ሰይፉ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የገቢ መሠረቶችን አሟጦ በመጠቀምና በመሠብሰብ የዞኑን የገቢ አቅም ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ የጋሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ አስተዳደር ከ114 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የጤና ጣቢያ የምረቃ ስነ-ስርአት እየተካሄደ ይገኛል
ኤንዞ ፌርናንዴዝ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በግል ጉዳዮች ከስምምነት ላይ ደረሰ!