የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርታማነታቸው የተረጋገጠ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ማሰራጨቱን አስታወቀ
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ደረጀ ቱሉ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ቴክኖሎጂ በማፍለቅ፣ በማስተዋወቅና በማላመድ ምርታማነታቸው የተረጋገጠ ዘጠኝ የቡና ዝርያዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል።
ቡና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ እንደመሆኑ ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር ምቹ የሆኑ 250 ሺህ ችግኞችን እና 40 ኩንታል የተለያየ ዝርያ ያለው የቡና ዘር ማሰራጨቱን ተናግረዋል።
በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የሕብረተሰብ ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ወጣቶችን፣ ሴቶችንና ሞዴል አርሶ አደሮችን በማደራጀት ስልጠናና ድጋፍ በመስጠት እንዲሁም ምርጥ ዘር በማቅረብ ከ500 ሺህ በላይ ችግኞችን በማሰራጨት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም አክለው ገልጸዋል።
በቀጣይም አቅርቦቱን የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራና ለደጋማ አየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችን በምርምር የማስፋፋት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
የቡና ችግኝ ሲወስዱ ያገኘናቸው አቶ ሙሉጌታ ማናዬ በሰጡት አስተያየት፤ በምርምር የተደገፉ ችግኞችን ከዚህ በፊት ወስደው የተከሉ መሆናቸውንና ከሌሎች ችግኞች ጋር ሲነጻጸሩ የተሻለ የዕድገት ደረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሌላኛው ተጠቃሚ አቶ ታረቀኝ ተንኬ በበኩላቸው፤ ሌሎች አርሶ አደሮች ከማዕከሉ ወስደው የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን በማየታቸው አሁን ለመትከል ችግኝ መውሰዳቸውን ገልጸው ችግኞችን በስፋት ለመትከል ቢፈልጉም አሁንም የአቅርቦት እጥረት መኖሩን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ: በዛብህ ታደሰ – ከማሻ ጣቢያችን

More Stories
የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች ለሀገር እድገት ወሳኝ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በደቡብ ኦሞ ዞን የማሌ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ
የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት በዞኑ ለሚከናወኑ ሥራዎች ከ10 ቢሊየን 7 መቶ 88 ሚሊየን 6 መቶ 12 ሺህ ብር በላይ በጀት አፀደቀ
በአሪ ዞን የባኮ ዳውላ ኣሪ ወረዳ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቀቀ