የዳውሮ ብሔር ዘመን መለወጫ “ቶክ በኣ” በዓል ባህልን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
በዓሉ በዞን በተለያዩ አካባቢዎች እየተከበረ ይገኛል።
በጨረቃ ኡደት በሚከናወነው በዳውሮ ብሔር ዘመን አቆጣጠር የሚከበረው “ቶክ በኣ” በዓል ተሸክሞ ማየት የሚል የቃል ፍቺ ያለው ሲሆን በአሮጌው አመት ሠርቶ በላቡ ከሰራው በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጠግቦ በልቶ ማደር እንደሚገባ የሚያስረዳ ነው።
በዓሉ በዞን ደረጃ ከመከበሩ ቀድሞ በየአካባቢዎች በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች የሚከበር ሲሆን በታርጫ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ቀበሌያትም ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ እየተከበረ ይገኛል።
በአሉ በአሮጌው አመት የተከሰቱ መጥፎ አጋጣሚዎች በአዲሱ እንዳይደገሙ፣ አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የልማትና የእድገት እንዲሆን በሀገር ሽማግሌዎች መልካም ምኞት ምረቃት ተደርጎበታል።
የሀገር ሽማግሌዎች በምርቃት ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት፤ የብሔሩ ማንነት መገለጫ “ቶክ በኣ” በዓል የተጣላ ታርቆ፣ የተለያየ ተሰባስቦ፣ ሰውና የቤት እንስሳት ጭምር ጠግበው የሚበሉበትና አዲሱ ዓመት የመልካም እንዲሆን የሚመረቅበት ነው።
በዓሉን ከህፃንነታቸው ጀምረው ከወላጆቻቸው ጋር እያከበሩ መምጣታቸውን አስታውሰው ትውልዱ የበዓሉን አከባበር በውል ተረድቶ ማስቀጠል እንደሚገባ የሀገር ሽማግሌዎቹ ተናግረዋል።
በዓሉ በአደባባይ ደረጃ መከበሩ የዞኑን ባህል፣ ታሪክና ቅርሶች በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው በመጠቆም “ቶክ በኣ” በአለም አቀፍ ደረጃ ተመዝግቦ የበለጠ እንዲታወቅና እንዲጠበቅ ሊሠራ እንደሚገባም ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጠቁመዋል።
የታርጫ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ናርሳ እንደገለፁት፤ የዳውሮ ብሔር በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊና ታርካዊ ቅርሶች ያሉት ሲሆኑ የዘመን መለወጫ ቶክ በኣ በዓልም ከእነዚህ ቅርሶች አንዱ ነው ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ታክስ መንደር በተካሄደው በዓል አከባበር ላይ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ብልፅግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበሻው ተፈራ፤ ቶክ በኣ የብሔሩ መገለጫና የዘመን መለወጫ በመሆኑ ሁሉም የብሔሩ ተወላጆች በአንድነት እያከበርን ባህላችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የጥንት አባቶችና እናቶቻችን አሮጌ ዓመትን ሸኝተው አዲሱን ዓመት በመልካም ምኞት የሚቀበሉት አንደሆነ ጠቁመው በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ እንዲመዘገብ እየተሠራ እንደሆነም ገልፀዋል።
የዳውሮ ብሔር ዘመን መለወጫ ቶክ በኣ በዓል አሁን ላይ በዞኑ በሚገኙ ቀበሌያት ደረጃ እየተከበረ ሲሆን በወረዳና ከተማ አስተዳደር ደረጃም እየተከበረ መጥቶ በዞን ደረጃም በከፍተኛ ድምቀት እንደሚከበርም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
የገቢ መሠረቶችን አሟጦ በመጠቀምና በመሠብሰብ የዞኑን የገቢ አቅም ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ የጋሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ አስተዳደር ከ114 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የጤና ጣቢያ የምረቃ ስነ-ስርአት እየተካሄደ ይገኛል
ኤንዞ ፌርናንዴዝ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በግል ጉዳዮች ከስምምነት ላይ ደረሰ!