የገቢ መሠረቶችን አሟጦ በመጠቀምና በመሠብሰብ የዞኑን የገቢ አቅም ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ የጋሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
በ2019 በጀት አመት ከ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሰብ ግብ ተጥሎ ወደ ስራ መገባቱን የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታውቋል።
መምሪያው የ2018 የግብር እቅድ አፈጻጸምና የ2019 በጀት አመት ዕቅድን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባምንጭ ከተማ እየመከረ ይገኛል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጋሞ ዞን አስተዳደሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ባለፉት ሁለት ተከታታይ አመታት በገቢ አፈጻጸም ውጤታማነት በክልል ደረጃ ዞኑ ተሸላሚ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊመሠገኑ እንደሚገባና በቀጣይም በተሻለና ባደገ መልኩ አፈጻጸሙ የተሳካ እንዲሆን የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል።
የገቢ ስራ የገቢ ተቋም ስራ ብቻ አለመሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር ደምስ፤ የገቢ አቅምን ለማሳደግና የታክስ ተገዥነትን ለማስፋት የባለሙያውንና የአመራሩን ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል።
የገቢ መሠረቶችን አሟጦ መጠቀምና መሠብሰብ እንደሚገባና የገቢ አገልግሎቱን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ለተገልጋዩ የዘመነ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ ሀላፊ አቶ ቶማስ ቶቤ በበኩላቸው፤ በ2018 በጀት አመት 4 ቢሊዮን 513 ሚሊዮን 781 ሺህ ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 4 ቢሊየን 619 ሚሊየን 365 ሺህ 311 ብር ገቢ በመሠብሰብ የእቅዱን 102 ነጥብ 34 ከመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
ለዕቅዱ መሳካት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለድርሻ አካላትን ያመሰገኑት አቶ ቶማስ፤ በሂደቱ ጠባቂነት፣ የገቢ አማራጮችን አሟጦ አለመጠቀምና ሌሎች ተግዳሮቶች የነበሩ ቢሆንም በዘንድሮው በጀት አመት ቀደም ሲል የታዩ ጉድለቶችን በማረም የግብር አፈጻጸሙን የተሳካ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በ2019 በጀት አመት 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ለመሠብሰብ ግብ ተጥሎ ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት የመምሪያው ሀላፊ፤ ለዕቅዱ መሳካት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብና ጥረት የሚጠይቅ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ አስተዳደር ከ114 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የጤና ጣቢያ የምረቃ ስነ-ስርአት እየተካሄደ ይገኛል
ኤንዞ ፌርናንዴዝ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በግል ጉዳዮች ከስምምነት ላይ ደረሰ!
የዳውሮ ብሔር ዘመን መለወጫ “ቶክ በኣ” በዓል ባህልን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ