የወባ ቅድመ መከላከል ስራ ውጤት እያስገኘ መምጣቱን በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች ተናገሩ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወባ ቅድመ መከላከል ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ በማከናወናቸው የበሽታው ስርጭት እየቀነሰ መምጣቱን በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ገለጹ፡፡
ዋና ዋና የወባ በሽታ ቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ህብረተሰቡ ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖረው ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የወረዳው ጤና ጽ/ቤት አስታውቋል።
ከዴቻ ወረዳ የቦባ-ገጫ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፍቅርተ አጣኖ እና አቶ ሽፈራው ሰርተት ለጣቢያችን በሰጡት አስተያየት ከሁለት አመት በፊት የወባ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ የጤና ጉዳት አድርሶቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ይሁንና የጤና ባሙያዎች ባደረጉት ጥብቅ ክትትልና ህብረተሰቡም በተሰጠው ግንዛቤ መሠረት የቅድመ መከላከል ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ማከናወን በመቻሉ ዘንድሮ በሽታው መቀነሱን ገልጸዋል፡፡
ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና የመድፈን ስራዎችን መስራታቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፥ ከጤና ባለሙያዎች የተሰጠውን ትምህርት ተግባራዊ በማድረግና የአልጋ አጎበር በአግባቡ መጠቀማቸው በሽታው እንዲቀንስ አድርጓል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሰላሙ ዳምጠው እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት አመት የወባ በሽታ ምልክት ታይቶባቸው ከተመረመሩት 14 ሺህ 542 የቀበሌ ነዋሪዎች መካከል ከ9 ሺህ በላይ የሆኑት ከወባ በሽታ ነጻ መሆናቸውን የምርመራው ውጤት ያሳያል ብለዋል፡፡
ይህም ካለፉት ሁለት አመታት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው ወባ በሽታ ሁኔታ ቀንሶ መታየቱን ጠቁመው፥ አሁንም ህብረተሰቡ የቅድመ መከላከል ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ዋና ዋና የወባ በሽታ ቅድመ መከላከል ሥራዎች የሚባሉትን ህብረተሰቡን ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖረው ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የዴቻ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማዬሁ ኬቶ፥ የዘንድሮ የወባ በሽታው ስርጭት መጠን እየቀነሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
ከ54 ሺህ በላይ የአልጋ አጎበር ለ24 ሺህ አባዎራዎች እና እማዎራዎች መሰራጨቱን ገልጸው፥ እየተሰጠ ካለው የግንዛቤ ትምህርት የተነሳ አጎበሩን የመጠቀም ልምድ በህብረተሰቡ ዘንድ እየዳበረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
የወባ መድሃኒትና አስፈላጊውን የህክምና ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ በወቅቱ እየተሰራ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡
ከሰኔ እስከ መስከረም ድረስ ያሉት ወራቶች ለወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኞች መራባት ምቹ በመሆኑ ሳይዘናጉ ነቅቶ የመከላከል ስራዎችን ህብረተሰቡ እንዲሰራ መክረዋል፡፡
ዘጋቢ: ሀብታሙ ታደሰ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል ድጋፍ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ ሩዝ ያመረቱ አርሶ አደሮች ምርታማ መሆናቸውን ገለፁ
በክልሉ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ እናቶችና ሴቶች ተደራሽ በማድረግ ጤናቸው እንዲጠበቅ በትኩረት መሠራቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ
የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ በመምጣታቸው የተሻለ የጤና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን በከምባታ ዞን አንዳንድ የዶዮገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች ተናገሩ