በቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ የማህበረሰቡ እንግልት መቀነሱ ተገለፀ

በቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ የማህበረሰቡ እንግልት መቀነሱ ተገለፀ

ሆስፒታሉ ከ110 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የጎፋ ዞን በቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ለማ በሰጡት አስተያየት ገለጹ።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጁ እንዳስታወቀው ሆስፒታሉ መደበኛ ስራ ከጀመረ በአራት ወራት ከ110ሺህ በላይ ለሚሆኑ የበቶ ከተማና የዑባ ደብረፀሐይ ወረዳ ነዋሪዎች እንዲሁም ለአጎራባች ወረዳ ቀበሌያት በስፋት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የመድኃኒት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ ከሁለት ጊዜ በላይ የመድሐኒት ግዥ ስራ ተከናዉኖ በአግባቡ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመዉ፥ አከባቢዉ ቆላማ በመሆኑ ሰፊ የዉሃ አቅርቦት የሚፈልግ ቢሆንም እጥረት ስለሚኖርና በጀኔሬተር የተደገፈ በመሆኑ ለከፍተኛ ወጪ ስለሚያዳርግ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከቱ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አቶ ኤልያስ አስረድተዋል፡፡

የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት እና የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አበል ወ/ጊዮርግስ እንደገለፁት፥ ሆስፒታሉ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ለድንገተኛ እና መደበኛ ታካሚዎች የህክምና አገልግሎት መስጠታቸዉን ጠቁመዉ፥ ሆስቲታሉ ቅድመ መከላከል እና አክሞ ማዳን ላይ በትኩረት ለይቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

በክረምት በጎ ስራ የግፊት፣ የስኳር፣ የቲቪ በሽታ እና ኤች.አይቪ ምርመራ እያካሄዱ መሆናቸውን አንስተው 340 ሰዎችን የደም ግፊት ምርመራ በማድረግ 18 ሰዎች ላይ በሽታው በመታየቱ ህክምና እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ሲስተር ምስጋና አድማሱ አዋላጅ ነርስ ሲሆኑ አንዲትም እናት በወሊድ ምክንያት እንዳትሞት ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ አስፈላጊውን የምክር አገልግሎቶች እና ምርመራዎችን እያካሄዱ መሆናቸውን አስረድተው፥ ወደ ጤና ተቋም ሳይመጡ ቤት የሚወልዱ እናቶች በከፍተኛ ቁጥር መቀነሱን ተናግረዋል።

በላቦራቶተሪ ምርመራ የወባ በሽታ፣ የኩላሊት፣ ሲ.ቢ.ሲ እና ሌሎች ምርመራዎች እንዲሁም በኤክስ ሬይ (X-ray) የጀርባ አጥንት፣ የአጥንት መሰበርና መመታት፣ የዲስክ መንሸራተት እና ሌሎች በርካታ ምርመራዎች እየተሰጡ መሆናቸዉን በሆስፒታሉ የላቦራቶሪ ባለሙያ ሳሙኤል አየለ እና ሜዲካል ሪዲዮሎጂ ቴክኖሎጅስት አገኘዉ ደርዘነ ተናግረዋል፡፡

ከፋርማሲ ባለሙያዎች መካከል ሙሉሰዉ አዝመራዉ እና መቅደስ መንገግስቱ የተለያዩ የመድኃኒት ዓይነቶች በተሟላ ሁኔታ ቢኖርም አከባቢው የወባ ስርጭት ከመኖሩ አካኳያ የወባ በሽታ መድኃኒት እጥረት መኖሩን ጠቁመው ለተገልጋዩ በቂ አገልግሎት እንዲኖር የመድኃኒት ግዥዎች እየተፈፀሙ መሆኑን አንስተዋል።

ካነጋገርናቸው ከወላድ እናቶች መካከል ጠጅቱ ቃኬ እና ወ/ሮ ጉጉቲ ኦኬ ከቅድመ ክትትል ጀምሮ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ እያደረጉ መቆየታቸው ተናግረው፥ የራሳቸውንና የልጃቸው ህይወት ደህና እንዲሆን የሆስፒታሉ መገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አንስተዋል።

ልጃቸዉን ለማሳከም የተገኙት ወ/ሮ አባይነሽ ክንቱ፣ አቶ ማላ ዱላ እና አቶ ኤርሚያስ ኤራዶ በጋራ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት ሆስፒታል በአቅራቢያ ባለመኖሩ ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ አባክነዉ ለብዙ ስቃይና እንግልት እየተዳረጉ መቆየታቸዉን አስታዉሰዉ አሁን በቅርበት በቂ አገልግሎት በማግኘታቸዉ መደሰታቸዉን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ :ኢያሱ አዲሱ – ከሳውላ ጣቢያችን