ምሁራን ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም ከአካባቢያቸው አልፈው ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ምሁራን ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም ከአካባቢያቸው አልፈው ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በኢፌዴሪ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን የገለጹት በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 4ኛው ዙር የኮንሶ ምሁራን ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው።
በጉባኤው ላይ የተገኙት አቶ ሰለሞን ሶካ፤ የምሁራን ተሰባስበው ለአካባቢያቸው፣ ለማኅበረሰባቸው እንዲሁም ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን ሚና መጫወት የሚችሉት ዕውቀታቸውንና ሀሳባቸውን በጥራት ማዋጣት ሲችሉ ብቻ በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል።
በተጨማሪም መንግሥትና ሲቪክ ማኅበራት ተናበው ሲሠሩ ሀገርን መለወጥ የሚቻል በመሆኑ በዚህ ረገድ በትጋት መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገለቦ ጎልቶሞ በበኩላቸው፤ ምሁራን ሀገርን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ በመመካከርና የማኅበረሰብን እድገት ወደኋላ ከሚመልሱ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ራሳቸውን በማራቅ ማኅበሩንና አካባቢውን የመለወጥ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጉማቾ ኩሴ፤ ማኅበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ማኅበረሰቡን የሚቀይሩ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ የተቋቋመበትን ዓላማ እውን ለማድረግ በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በጉባኤው ላይ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች የሚቀርቡ ከመሆኑም በላይ የማኅበሩ አፈጻጸምና የቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡ ሲሆን፤ በስብሰባው የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የማኅበሩ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ: አማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
ሳውላ ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተካሄደ ነው
የዝናብ እጥረት የቡና ምርትን እንዳይጎዳ የማሳ እርጥበትን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
ማህበረሰብ አቀፍ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ዘላቂ ውጤት እስኪመዘገብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ