የአርሰናሉ ኮከብ አዲስ ተስፋና ተነሳሽነት

የአርሰናሉ ኮከብ አዲስ ተስፋና ተነሳሽነት

በሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል እና በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የ24 ዓመቱ የክንፍ መስመር ተጫዋች ቡካዮ ሳካ፣ ከጉዳት መልስ አዲስ የብቃት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በማሳየት ላይ ይገኛል።

ባለፈው የውድድር ዘመን የመጨረሻ ወራት ገጥሞት በነበረው ጉዳትና የተወሰነ የጨዋታ ጊዜ ማጣት ቢኖርም፣ ሳካ አዲሱን የፕሪምየር ሊግ ውድድር ዘመን በከፍተኛ ተነሳሽነት ጀምሯል።

በመክፈቻው ጨዋታ አርሰናል አዲስ አዳጊውን ኮቨንትሪን 3 ለ 0 በረታበት ጨዋታ ላይ ሳካ ያሳየው አስደናቂ እንቅስቃሴና ያስቆጠራት ግብ፣ ተጫዋቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ደረጃው መመለሱን አመላክቷል።

ሳካ ባለፈው መጋቢት ወር በገጠመው ጉዳት ምክንያት ሰባት የአርሰናል ጨዋታዎችና ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ካመለጡት በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ አርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ሆኖም በቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ አርሰናል በፒኤስጂ ሲሸነፍና በዓለም ዋንጫው የእንግሊዝ አሰልጣኝ ቶማስ ቱከል የጨዋታ ደቂቃውን ሲቀንሱበት ተጫዋቹ የብቃቱ ጣራ ላይ እንዳልነበረ ታውቋል።

ምንም እንኳን በዓለም ዋንጫው የነበረው የጨዋታ ጊዜ 48 በመቶ ብቻ ቢሆንም፣ በቡድኑ ከፍተኛውን ሶስት ግብ የሆኑ የመጨረሻ ኳሶችን እና ሶስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

በተለይም እንግሊዝ ፈረንሳይን 6 ለ 4 አሸንፋ 3ኛ ደረጃን በያዘችበት ጨዋታ ላይ ያስቆጠረው ‘ሀት-ትሪክ’ አስደናቂ ተጫዋችነቱን ያሳየበት ነበር።

ከዓለም ዋንጫው በኋላ የሰባት ቀናት እረፍት ብቻ በመውሰድ በፍጥነት ወደ ልምምድ የተመለሰው ሳካ፣ ለበሰጠው አስተያየት “የዓለም ዋንጫው ለእኔም ሆነ ለቡድኑ ባሰብነው መንገድ አልሄደም። ከውድድሩ በኋላ በጣም ተራብኩኝ፤ አዲሱን ውድድር ዘመን በጉጉት ነበር የምጠብቀው። ሰውነቴ በከፍተኛ ብቃት ላይ እንዲገኝ ጠንክሬ ሠርቻለሁ” ሲል ተናግሯል።

የሳካ ወደ ከፍተኛ ብቃት መመለስ ከጉዳት ነፃ ከሆኑት የቡድን አጋሮቹ — ቤን ዋይት፣ ማርቲን ኦዴጋርድ እና ካይ ሀቨርትዝ ጋር መጫወቱ ጋር የተያያዘ ነው።

በተለይም ከቤን ዋይት ጋር በቀኝ ክንፍ የሚያደርጉት ጥምረት የአርሰናል የማጥቃት መስመር ዋነኛ መሳሪያ ነው።

ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት 153 ጨዋታዎችን ያደረገው ሳካ፣ አሁን ያገኘው አጭር እረፍትና ሙሉ ጤንነት አርሰናል የፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ጉዞውን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ለዋንጫው ዋና ተፎካካሪ እንዲሆን ትልቅ አቅም እንደሚሆነው ይታመናል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ