በጎፋ ዞን ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ በጎፋ ዞን ለአቅመ ደካሞች አራት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
“ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በጎፋ ዞን በላሃ ከተማ፣ በመሎ ኮዛ ወረዳ እና በመሎ ጋዳ ወረዳ በአጠቃላይ አራት ደረጃቸውን የጠበቁ የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለአቅመ ደካሞች ለማስረከብ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሪሁን ፍቅሩ፥ የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆነውን የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ በክልሉ ግብርና ቢሮና ተጠሪ ተቋማት አጠቃላይ ወጪ ማስጀመራቸውን አስረድተዋል።
በላሃ ከተማ ሁለት፣ በመሎ ኮዛ ወረዳ አንድ እና በመሎ ጋዳ ወረዳ አንድ በድምሩ አራት ቤቶች በቢሮው ወጪ እየተገነቡ ሲሆን፥ ቤቶቹ ከሙሉ የቤት ቁሳቁስ ጋር ተጠናቀው በቅርቡ ለተጠቃሚዎቹ እንደሚተላለፍ ዶ/ር መሪሁን ተናግረዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው “በጎነት የጋራ ዕሴት ነው” መሆኑን ጠቁመው፥ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር በዞኑ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውና የክልሉ ግብርና ቢሮ በዞኑ ተገኝቶ ለአቅመ ደካሞች ቤት ለመገንባት በመምረጡ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
የቤት ግንባታ የተጀመረላቸው አረጋውያንም ለተደረገላቸው ድጋፍና ትብብር ከልብ ምስጋና አቅርበው፥ መንግሥትና ሕዝብ ለአቅመ ደካማ አረጋውያን እያደረጉ ያለውን ሰብዓዊ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ — ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የትጋት አክሊል የደፋው የሆሳዕናው ወጣት የሮቤል ጌታቸው የድል ጉዞ
የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የተለያዩ የመረጃ አማራጮችን በመጠቀም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ወቅታዊ፣ ሚዛናዊና ተዓማኒነት ያለው መረጃ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ