ማንቼስተር ሲቲ አዩብ ቡአዲን አስፈረመ

ማንቼስተር ሲቲ አዩብ ቡአዲን አስፈረመ

ማንቼስተር ሲቲ የመሃል ሜዳ ክፍሉን እንደገና ለመገንባት በሚያደርገው ሰፊ እንቅስቃሴ የሊል እና የሞሮኮውን ድንቅ አማካይ አዩብ ቡአዲን በታሪካዊ የ86 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሒሳብ ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል።

እንደ ስካይ ስፖርትስ ዘገባ ከሆነ ማንቼስተር ሲቲ 81.3 ሚሊዮን ፓውንድ ቀጥታ ክፍያ የሚያከናውን ሲሆን ተጨማሪ 4.3 ሚሊዮን ፓውንድ ደግሞ ከአፈፃፀም ጋር በተያያዙ መስፈርቶች (add-ons) የሚከፈል ይሆናል።

ወጣቱ ኮከብ እ.ኤ.አ እስከ 2031 ክረምት ድረስ በክለቡ የሚያቆየውን የ5 ዓመት ኮንትራት ተፈራርሟል።

ይህ ዝውውር አዩብ ቡአዲን ሌላኛውን የቀድሞ የሊል ተጫዋች ሌኒ ዮሮን ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሲያመራ ከወጣበት 58.9 ሚሊዮን ፓውንድ በመብለጥ በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ውዱ ታዳጊ ተጫዋች ያደርገዋል።

በክረምቱ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ከሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ጋር ደማቅ ብቃት በማሳየት የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ቡአዲ፡ ሊል ለዝውውሩ ሲጠይቀው የነበረውን ሙሉ የዝውውር ሂሳብ በማስገኘት የፈረንሳዩን ክለብ ጥያቄ አሟልቷል።

እንደ ሮድሪ፣ በርናርዶ ሲልቫ እና ቲጃኒ ሬይንደርስ ያሉ ቁልፍ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች ስንብት ተከተሎ፡ የኤንዞ ስብስብ ቡድኑን እንደገና የማደራጀት ትልቅ ስራ ላይ ይገኛል።

የ18 ዓመቱ ቡአዲም የዚህ አዲስ የመሃል ሜዳ ፕሮጀክት ዋና ማዕከል እንደሚሆን ይጠበቃል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ