የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሁሉም መስክ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የደቡብ ኣሪ ወረዳ ምክር ቤት ገለጸ።
የደቡብ ኣሪ ወረዳ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት 29ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡
የወረዳው ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሀገሬ ጥላሁን በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ማህበረሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በጥንካሬ የተመዘገቡ ተግባራትን በማስቀጠልና ውስንነቶችን በማረም በበጀት አመቱ በሁሉም መስኮች የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የደቡብ ኣሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገብሬ ባይስማይ በበኩላቸው፥ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀመሩ የመንገድ ከፈታ ስራዎች፣ በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ፣ ጠንካራ አፈጻጸሞችን በማስቀጠል ሌሎች በጉድለት የተገመገሙ ተግባራትን በራስ አቅም በመፈፀም ከወረዳው አቅም በላይ የሆኑ የመብራት፣ የኔቶርክና የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የበጀት ረቂቅ ያቀረቡት የደቡብ ኣሪ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የመንግስት ፋይናንስ አስተባባሪ አቶ ብቻውን ገዛኸኝ፥ የበጀት ዓመቱ ረቂቅ በጀት በዝርዝር ከተገመገመ በኋላ የወረዳው በጀት 593 ሚሊየን 226 ሺ ከ72 ብር ሆኖ እንዲጸድቅ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት በወረዳው በርካታ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው፥ በውስንነት የተገመገሙትን አስፈፃሚ አካላት በትኩረት በመስራት የወረዳውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር በወረዳው ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ ጥያቄዎችን በአባላቱ ቀርቦ ምላሽና ማብራርያ ተሰጥቶባቸዋል።
በተያያዘ ዜና የምክር ቤቱ አባላትና ተሳታፊዎችም በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ በተለይ በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ የሚያስችል የደም መለገስ መርሃ ግብርም አካሂደዋል።
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ማህበረሰብ አቀፍ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ዘላቂ ውጤት እስኪመዘገብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
የትጋት አክሊል የደፋው የሆሳዕናው ወጣት የሮቤል ጌታቸው የድል ጉዞ
በጎፋ ዞን ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ