የትጋት አክሊል የደፋው የሆሳዕናው ወጣት የሮቤል ጌታቸው የድል ጉዞ
ከትጋትና ቁርጠኝነት ማህፀን የሚወለድ ስኬት የሰውን ልጅ ማንነት ከፍ ከፍ ሲያደርግ መመልከት ሁሌም ቢሆን ልብ ይነካል፤ ኩራትም ያጎናጽፋል። በተለይ በተለያዩ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈው፣ የሌሊት እንቅልፋቸውን መስዋዕት አድርገው በውጤታቸው የነገዋን ኢትዮጵያ ተስፋ የሚያበሩ ወጣቶችን ታሪክ መስማት ለሀገር ትልቅ ብስራት ነው።
ዛሬም በዚሁ የድል አውድማ ላይ ለብዙዎች አርዓያ የሚሆን፣ በጽናትና በትጋት የደመቀ አንድ የብርሃን አበባ ታሪክ ተሰንዷል።
በሀዲያ ልማት ማህበር ስር በሚገኘው በሆሳዕናው የሊች ጎጎ አዳሪ ትምህርት ቤት የተኮተኮተው ኮከብ ተማሪ ሮቤል ጌታቸው፥ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና 590.08 አስደናቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
ሮቤል በዚህ የላቀ ውጤቱ ከሀገር አቀፍ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ፣ ከተመዘገበው የሀገሪቱ ከፍተኛ ውጤት በ1 ነጥብ ብቻ ዝቅ በማለት የድል አክሊሉን በኩራት ደፍቷል።
ይህን ብርቱ ፈተና ሰብሮ የወጣው ወጣት የስኬት ምስጢር ከልጅነቱ ጀምሮ ለዕውቀት የሰጠው ልዩ ፍቅር፣ ራሱን የገራበት የጥናት ስልትና ያልበገረው ቁርጠኝነት ነው።
ሮቤል ለዚህ ማዕረግ ይበቃ ዘንድ የመምህር አባቱና የመላው ቤተሰቡ ተጋድሎና የማይናወጥ ድጋፍ መሪ ብርሃን እንደሆነው በትህትና ያሰምርበታል። ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን መኖሪያ ቤቱም የዕውቀት ማዕድ ሆኖ እንደቀረጸው ምስክርነቱን ይሰጣል።
“ወጣቶች አሉታዊ ተጽዕኖዎችን እና ‘የተማረ ሰው የት ደረሰ?’ የሚሉ ተስፋ አስቆራጭ ንግግሮችን ወደ ጎን በማለት፣ እይታቸውን በሚወዱት ዓላማና ግብ ላይ ብቻ ማድረግ አለባቸው።” ሲል ሮቤል ጌታቸው ምክሩን አጋርቷል፡፡
ለብዙዎች አስፈሪና አሰልቺ እንደሆነ የሚነገረውን የፊዚክስ ትምህርት 100 በመቶ ሙሉ ውጤት በማምጣት፣ ውስብስብ የሂሳብና የሳይንስ ቀመሮችን በትጋት ሰብሮ ማለፍ እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል።
የነገው ህልሜ በአቪዬሽንና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ አመርቂ ውጤት ማምጣትና መስራት መሆኑን ጠቁሞ፥ የዛሬው ስኬቴ የወደፊት ታላቅ ህልሜ መነሻ እንጂ መድረሻ አለመሆኑን አመላክቷል።
ወጣቱ ተማሪ ወደፊት ከፍተኛ ትምህርቱን በአቪዬሽን ዘርፍ ወይም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) በመቀሰም፣ ያገኘውን ዕውቀት ለሀገሩ እድገትና ከፍታ ለማዋል አልሞ ተነስቷል።
የሮቤል የዛሬ ውጤት የቤተሰቦቹ ብቻ ሳይሆን የሆሳዕና፣ የሀዲያና የመላዋ ኢትዮጵያ ኩራት ነው። በትጋት ለተጓዘ ወጣት የትኛውም ተራራ ቁልቁለት፣ የትኛውም መንገድ እሾሃማ እንደማይሆን ያስመሰከረ የዘመናችን አርዓያ ነው።
አዘጋጅ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ማህበረሰብ አቀፍ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ዘላቂ ውጤት እስኪመዘገብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
በጎፋ ዞን ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ