የአርባምንጭ ከተማ ሰላማዊና በተፈጥሮ ፀጋ የበለፀገለች መሆኗ ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ያደርጋታል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ

የአርባምንጭ ከተማ ሰላማዊና በተፈጥሮ ፀጋ የበለፀገለች መሆኗ ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ያደርጋታል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርባምንጭ ከተማ ሰላማዊና በተፈጥሮ ፀጋ የበለፀገለች መሆኗ ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ያደርጋታል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ተናገሩ፡፡

በ2018 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ 700 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የአርባምንጭ ከተማ ቱሪዝም መምሪያ አሰታውቋል፡፡

ለከተማው ልማትና አከባቢ ጥበቃ ስራዎች ከተሰጠው ትኩረት አኳያ ለጎበኚዎች ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ መደሰታቸውን አንዳንድ ጎበኚዎችና የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ከአርባምንጭ ከተማና ከጋሞ ዞን ልዑካን ጋር ተዘዋውረው የጎበኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ አከባቢው በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ፣ ሰላማዊና ቢጎበኙት የማይጠገብ መሆኑን ገልፀው፥ የቱሪዝም ልማቱን ከአከባቢ ጥበቃ ሥራዎች ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአርባምንጭ ከተማ ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ ደምበላ በበኩላቸው፥ የቱሪስት ፍሰት በከተማው ከዓመት ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረው፥ በ2018 በጀት ዓመት ከ364 ሺህ 827 የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎበኚዎች መጎበኘታቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 701 ሚሊዮን 81 ሺህ ብር ገቢ መሰብሰቡንም ኃላፊው ጠቁመው፥ ከተማውን የቱሪዝም ኮንፈረንስ ለማድረግ ታቅዶ በተሰራው ስራ የጎበኚዎች የቆይታ ዕድሜ በአማካይ ከ 3 ቀናት ወደ 5 ቀናት ማደጉን አቶ ደስታ ተናግረው አከባቢ ጥበቃና ቱሪዝም ልማቱን ለማስተሳሰር ታቅዶ እተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከከተማ ነዋሪዎችና ጎበኚዎች መካከል አንዳንዶች እንደገለፁት ለከተማው ልማትና ለአከባቢ ጥበቃ ስራ ከተሰጠው ትኩረት የተነሳ ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው የጎበኚዎች ቁጥር ከመጨመሩም ባሻገር ነዋሪው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ተነሳ ተረፈ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን