የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የተለያዩ የመረጃ አማራጮችን በመጠቀም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ወቅታዊ፣ ሚዛናዊና ተዓማኒነት ያለው መረጃ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ
የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ፤ ሚዲያ ዞኑ እየተሰሩ ባሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ህዝብና መንግስትን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የማህበረሰቡ የዘመናት ጥያቄ የነበረው የቴሌቪዥን ጣቢያ ምላሽ እንዲያገኝ በተለየ መልኩ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ ጀፎረን ጨምሮ በርካታ ያልታዩና ያልተጎበኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህ ሃብቶችን በማልማት በሃገር ደረጃ እንዲታወቁ በባለቤትነት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሚዲያ ለልማትም ሆነ ለጥፋት ያለው ጉልበት ከፍተኛ በመሆኑ ልማታዊ እሳቤ ላይ የተመሰረተና በጥራት ላይ ያተኮረ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የተለያዩ የመረጃ አማራጮችን በመጠቀም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ወቅታዊ፣ ሚዛናዊና ተዓማኒነት ያለው መረጃ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ ሸምሱ አማን፤ ሀገራችን በ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ተቋማቸው ጥራት ያለው መረጃ ለማሰራጨት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመለየት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በቀጣይም በመዋቅሮች አካባቢ የሚታዩ ውስንነቶችን ለይቶ እልባት በመስጠት ተከታታይነት ያላቸው ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አመላክተዋል።
የዞኑ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሃዲሞ ሃሰን፤ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሚከናወኑ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን በመግለጽ በቀጣይም ማህበረሰቡን የሚመጥኑና ትውልድ ተሻጋሪ ተግባራትን መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መምሪያው መረጃን ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ለስራ ማነቆ የሆኑ የግብዓትና የባለሙያ ውስንነቶችን በመቅረፍ በጥራት ላይ የተመሰረተ መረጃ ለህዝብ ማድረስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወ/ማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የንብረት ግዥን አስመልክቶ ከክልሉ መንግስት የተሰጠ መግለጫ
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ተቋማት በመንግስት እና በህዝብ መካከል የመረጃ ግልፀኝነት በመፍጠር የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት በውጤታማነት እንዲፈፀሙ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ
በተጠናቀቀው በጀት አመት እንደሀገርም ሆነ ልዩ ወረዳ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ