በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የንብረት ግዥን አስመልክቶ ከክልሉ መንግስት የተሰጠ መግለጫ
በቅርቡ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆች እና በመገናኛ ብዙሃን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ በፕሮግራም በጀት የተፈፀመን የንብረት ግዥ አስመልክቶ በስፋት እየተሰራጨ ያለውን መረጃ የክልሉ መንግስት በቅርበት እና በትኩረት ሲከታተለው ቆይቷል።
መንግስት የህዝብን ሀብት በአግባቡ፣ በቁጠባና ለታለመለት አላማ ብቻ ስራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ ዋነኛ ሀላፊነቱ መሆኑን በመገንዘብ፣ ከህዝብ የቀረበለትን ይህንን ጥቆማ በበጎ እና በከፍተኛ ሀላፊነት ተቀብሎታል። መንግስት ለጉዳዩ የሰጠውን አጽንኦት ተከትሎ፣ ይህንኑ ጉዳይ በጥልቀት በማየት ህጋዊነቱንና አሰራሩን የሚያጣራ የሚመለከታቸው የፍትህ፣ የኦዲት እና የፀረ-ሙስና አካላትን አደራጅቶ ወደ ምርመራ ስራ መግባቱን ማሳወቅ እንወዳለን።
ከዚህ ጎን ለጎን ጉዳይ ተጣርቶ በመንግስትና በፓርቲ አሰራር መሰረት ተገቢዉ ህጋዊ፣አስተዳዳራዊና ፖለቲካዊ ርምጃ እስኪወሰድ በደረሰዉ ጥቆማና በአጠቃላይ አመራር ግምገማና ምዘና መድረኮች በተነሱ ጭብጦች መነሻ በጉዳዩ የተጠረጠሩ 3(ሦስት) አመራሮችን ከዛሬ ጀምሮ ከኃላፊነታቸው እንዲታገዱ ተደርጓል።
በመሆኑም አሁን የተጀመረው ማጣራት እና ምርመራ እንደተጠናቀቀ፣ ከምርመራው በሚገኘው ውጤት ላይ ተመስርተን የህዝብና የመንግስትን ሀብት ባባከነ እና አግባብነት የጎደለው አሰራር በፈፀመ ማንኛውም አካል ላይ መንግስት የማያዳግም ህጋዊ፣ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ርምጃ የሚወስድ መሆኑን በፅኑ እናረጋግጣለን።
የህዝብ ሀብት የህዝብ ነው፤ ማንም ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ እና የተጠያቂነት ስርዓትን የማስፈን ጽኑ አቋማችንም በተግባር የሚቀጥል ይሆናል።
የክልሉ መንግስትም በመንግስትና በፕሮግራም በጀት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ጠብቅ ያለ ክትትል የሚያደርግ መሆኑን እንገልጻለን።
በዚህ አጋጣሚ የክልላችን ህዝብ የልማቱ እና የመልካም አስተዳደር ባለቤት በመሆን ሀብቱ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል ለሚያሳየው በሳል የዜግነት ግዴታ፣ እያደረገ ላለው የነቃ ተሳትፎ እና ጥረት የክልሉ መንግስት የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል።
የህዝብ ንቁ ተሳትፎ ለስርዓታችን ጤናማነት ወሳኝ ምሰሶ መሆኑንም የክልላችን መንግስት ያምናል።
በቀጣይም ህዝቡ ይህንን የጀመረውን በጎ ልምድ በማስቀጠል ከመንግስት ጎን በመቆም፣በእዉነተኛ መረጃ ላይ በመመስረት ብልሹ አሰራሮችን በመጠቆምና በማጋለጥ እንዲሁም ጉዳዩን ለሚያጣሩ የፍትህ አካላት ተገቢውን መረጃ በመስጠት የተለመደ ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችንን በታላቅ አክብሮት እናስተላልፋለን።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት

More Stories
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ተቋማት በመንግስት እና በህዝብ መካከል የመረጃ ግልፀኝነት በመፍጠር የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት በውጤታማነት እንዲፈፀሙ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ
በተጠናቀቀው በጀት አመት እንደሀገርም ሆነ ልዩ ወረዳ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ
በወረዳው በእናቶች እና የህጻናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፈ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ