አርሰናል ከ ላምፓርዱ ኮቨንተሪ ሲቲ
የ2026/27 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ዛሬ ምሽት 4:00 ላይ በሚደረግ የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል።
የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል በሜዳው ኤሚሬትስ ስታዲየም ከረዥም ጊዜ በኋላ ወደ እንግሊዝ እግር ኳስ ማማ የተመለሰውን ኮቨንተሪ ሲቲን ያስናግዳል።
ይህ ጨዋታ የውድድር አመቱ መክፈቻ ከመሆኑ ባሻገር በሁለቱ ቡድኖችና አሰልጣኞች መካከል ባለው ልዩ ትስስርና ታሪክ ምክንያት የብዙዎችን ቀልብ ስቧል።
ባለፈው የውድድር ዘመን ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ዘውድ የተቀዳጀው አርሰናል፣ ዘንድሮም የዋንጫ ክብሩን ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጉዞ የመጀመርያውን ሶስት ነጥብ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባል።
ስፔናዊው አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ በጠንካራ የተከላካይ ክፍላቸው እና በተደራጀው የቡድን መንፈሳቸው ላይ ተመስርተው የውድድር ዘመኑን በድል ለመጀመር ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከ25 ዓመታት ረጅም የቆይታ ጊዜ በኋላ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለመመለስ በቅቶ ታሪካዊ ስኬት ያስመዘገበው ኮቨንተሪ ሲቲ፣ ወደ ሰሜን ለንደን የሚያደርገው ጉዞ ቀላል እንደማይሆን ይታወቃል።
የቀድሞ የቼልሲ ዝነኛ ተጫዋች እና አሰልጣኝ የነበረው ፍራንክ ላምፓርድ ኮቨንተሪን ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ ይዘው ከመጡ በኋላ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከቀድሞ ተፎካካሪያቸው አርሰናል ጋር ማድረጋቸው ጨዋታውን የበለጠ ትኩረት የሚስብ አድርጎታል።
ላምፓርድ በሰሜን ለንደን በሚያደርገው የዛሬ ምሽት ፍልሚያ፣ ለአርሰናልና ለአርቴታ ቀላል የማይባል ፈተና ለመደቀን እና በፕሪሚየር ሊጉ መመለሳቸውን በጠንካራ ውጤት ለማብሰር አልመው ዘደ ሜዳ ይገባሉ።
በሁለቱ ክለቦች መካከል ረጅም ታሪክ ያለው ግንኙነት ቢኖርም፣ አርሰናል የበላይነቱን ይዞ ይገኛል።
ከአሁን ቀደም በሁሉም ውድድሮች 76 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አርሰናል 43 ጊዜ በማሸነፍ ነው የበላይነቱን የያዘው።
14 ጨዋታዎችን ደግሞ ኮቬንትሪ ሲያሸንፍ 19 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
ክለቦቹ ኮቨንተሪ ከሊጉ ከወጣ በኋላ በካፕ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አርሰናል በ2012 (6-1) እና በ2014 (4-0) አሸንፏል።
በፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ግንኙነታቸው እ.ኤ.አ በየካቲት 2001 ሲሆን አርሰናል ዴኒስ ቤርካምፕ ባስቆጠራት ግብ 1-0 አሸንፎ ነበር።
ኮቨንተሪ በአርሰናል ሜዳ የመጨረሻውን ድል ያስመዘገበው እ.ኤ.አ በነሐሴ 1993 የመክፈቻ ጨዋታ ላይ በሚኪ ኩዊን ሀትሪክ 3-0 ባሸነፈበት ወቅት ነው።
ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ
አርሰናል ከ ላምፓርዱ ኮቨንተሪ ሲቲ

More Stories
አርሰናል ኤዝሪ ኮንሳን በ55 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ አስፈረመ
ቶተንሃም ሳቪንሆን በ85 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ከስምምነት ደረሰ
አርሰናል ኤዝሪ ኮንሳን ለማስፈረም ከጫፍ ደረሰ