የአርሶ አደሩን የመሬት ሀብት ከፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር አርሶአደሩ የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርሶአደሩን የመሬት ሀብት ከፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር አርሶአደሩ የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሬት አስተዳደር ቢሮ ገልጿል፡፡
ፋይዳ መታወቂያ፣ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓትና የፋይናንስ አቅርቦት፣ የጎጂ መሬት አጠቃቀምና ቁጥጥር እና የመሬት ሀብት ቆጠራ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ፤ የአርሶአደሩን የመሬት ሀብት ከፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር አርሶአደሩ የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆን ጠንካራ ንቅናቄ መጀመሩን ገልጸዋል።
የመሬት አስተዳደርን ማሻሻል ለኢኮኖሚያዊ እድገት ለምግብ ዋስትና እና ለማህበራዊ መረጋጋት መሠረት መሆኑንም ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው እንዳሉት፤ መሬት ውድ እና ውስን ሀብት በመሆኑ በአግባቡ ሊያዝ እንደሚገባ አፅንኦት ተሰጥቷል።
አርሶአደሩ የመሬት ሀብቱን በመጠቀም የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን በመጠቆም መሬት ተቆጥሮ እና ከፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ጋር ተሳስሮ መያዝ አለበት ብለዋል።
በመድረኩ የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰብስቤ ቡናቤን ጨምሮ ከ12ቱ ዞኖች የተውጣጡ የመሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊዎች፣ ከ3ቱ ሪጂዮ ፖሊስ ከተማ ተጠሪዎች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ: አስናቀ ካንኮ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የአፈር ጤናን በመጠበቅና ለምነትን በማሻሻል የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ይሠራል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
ጥራቱ የተጠበቀ ከ500 ቶን በላይ እሸት ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ