የክልሉ ሕዝቦች ሰላምና አንድነት እንዲጎለብት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ገለጹ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን በቴፒ ከተማ አካሂዷል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ አቶ መሰለ ከበደ፥ ጉባኤው የ7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በስኬት በተጠናቀቀ ማግስት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የክልሉን የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ለዘመናት የቆዩ የግጭት መንስኤዎችን በውይይትና በምክክር ለመፍታት ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልፀው፥ ይህም የሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ምክትል አፈ-ጉባኤው ጠቁመዋል።
በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመከተልና በሁሉም መዋቅሮች ውስጥ ግንዛቤ በመፍጠር ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ቀድሞ የማስቀረትና የሕዝቦችን አንድነት የማጠናከር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የምክር ቤቱን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንደሻው በበኩላቸው፥ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተመጣጣኝ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል ሥራ መሠራቱንና የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ለማቋቋም የሚያስችል የሰነድ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የሕገ-መንግሥቱን የበላይነት በማረጋገጥና የብሔረሰቦችን መብት በማስከበር ወንድማማችነት እንዲጎለብት፣ ዘላቂ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለይቶ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በክልሉ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተው በተለያዩ ተቋማትና አካባቢዎች በዓሉን በስኬት ማክበር መቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ ሕገ-መንግሥት ዙሪያ፣ ስለ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ግንዛቤ ለመፍጠር ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፥ የፌዴራሊዝም ጽንሰ-ሀሳብ፣ የግጭት አፈታትና በብሔረሰቦች ዕሴቶች ዙሪያ የሚያስተምሩ ፕሮግራሞች በሦስት የኤፍ.ኤም (FM) ሬዲዮ ጣቢያዎች በ11 የክልሉ ብሔረሰቦች ቋንቋዎች እንዲሰራጩ መደረጉንም አስረድተዋል።
በምክር ቤት አባላት ለቀረቡት ጥያቄ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን የ2019 የምክር ቤቱ ጠቋሚ ዕቅድን በማፅደቅ ጉባኤው ተጠናቋል።
ዘጋቢ: በዛብህ ታደሰ – ከማሻ ጣቢያችን

More Stories
የአፈር ጤናን በመጠበቅና ለምነትን በማሻሻል የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ይሠራል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
ጥራቱ የተጠበቀ ከ500 ቶን በላይ እሸት ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ