የኮንታ ዞን ም/ቤት 4ኛ ዙር 4ኛ ሥራ ዘመን 26ኛው መደበኛ ጉባኤው ተጠናቀቀ

የኮንታ ዞን ም/ቤት 4ኛ ዙር 4ኛ ሥራ ዘመን 26ኛው መደበኛ ጉባኤው ተጠናቀቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኮንታ ዞን ምክር ባካሄደው 4ኛ ዙር 4ኛ የስራ ዘመን 26ኛ መደበኛ ጉባኤ ከ2 ቢሊዮን 606 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ አጠናቋል::

የዞኑ ም/ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ብርሃኑ አቱሞ ም/ቤት የዞኑ መንግስት ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት በመሆኑ፥ ለዞኑ ህብረተሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት የሚያፋጥኑ ህጎችን በማውጣት የመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራዎች ሲከናወኑ የዜጎች መብቶችና ነፃነቶች መከበርና የመልካም አስተዳደር መስፈኑን የሚያረጋገጡ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በርካታ ሀገራዊና ክልላዊ ተልዕኮች የተፈፀሙበት ዓመት ቢሆንም፥ ም/ቤቱ የሚቆጠሩ ተግባራትን ማከናወኑን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል።

የዘንድሮን ጉባኤ ልዩ የሚያደርገው አገራዊና ክልላዊ ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ፍትሃዊ፣ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ በስኬት በተካሄደበትና ኢትዮጵያ በታሪኳ በሀሳብ ልዕልና ላይ በመመስረት ተወካዮቿን በመሰብሰብ ሀገራዊ ምክክር እያካሄደች ባለችበት ጊዜ ላይ መካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ በበኩላቸው፥ እንደ አገራችን ብሎም በዞናችን ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት ዓመታት መሆናቸውን ተናግረው፥ የሚሠሩ ሥራዎች የአገሪቱ የልማት አቅጣጫዎችን በመከተል የህዝብ ጥያቄዎችንና ፍላጎቶችን መሠረት በማድረግ በተሠራው ሥራ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ዘንድሮ በመሠረተ ልማት ሥራዎች ትልቅ ትኩረት በመስጠት በመንገድ መሠረተ ልማት መስፋፋት፣ ለግብርና፣ ለጤናና ለትምህርት ሥራዎች መሳለጥ ትልቅ ሚና ስላለው በአጠቃላይ በዞን ደረጃ ወደ 170 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ መሥራት መቻሉን አስረድተዋል።

የግብርናው ዘርፍ የላቀ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆኑ የአርሶ አደርን ኑሮ ደረጃ እንዲያሻሻል በተላይ የቡና ምርትን ለማሳደግ ዘንድሮ 7.5 ሚሊዮን የቡና ችግኝ በማዘጋጀት መተከሉን ጠቁመው፥ በቀጣይ መንግሥት በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ የህዝብ ተሳትፎ ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥተው እንደሚሠራ አቶ ታከለ ተናግረዋል።

ካነጋገርናቸው የም/ቤት አባላት መካከል አቶ አያሌው ከበደ፣ ወንድሙ ወጁና ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ በዞኑ በሁሉም ዘርፎች እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች የተሻለ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑ፥ በተለይ በመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች ዞኑን ካለው አቅም ተወዳዳሪ ማድረግ የሚችሉና የህዝብን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች የመለሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የኩታ ገጠም እርሻ በቡና ምርት ላይ እየታዩ ያሉ ለውጦችን በማጠናከር አካባቢው ለምርትና ምርታማነት ምቹ በመሆኑ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅምን ለማሳደግ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ላይ በትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል።

ጉባኤው ለ2019 በጀት ዓመት ስራ ማስፈፀሚያ 2 ቢለዮን 606 ሚለዮን 647 ሺህ 885.27 ብር በጀት ቀርቦ ተወያይቶ በማፅደቅ ተጠናቅቋል፡፡

ዘጋቢ፡ ብርሃኑ ግንበቶ – ከዋካ ጣቢያችን