መስራት እየቻሉ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች ለመፍታት የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ቀላል አለመሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) መስራት እየቻሉ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች ለመፍታት የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ቀላል አለመሆኑን የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ ገለጹ፡፡
አስተማማኝ የቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ስራ ማህበር በሚዛን አማን ከተማ ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ ማህበሩን መርቀው በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በዞኑ የህብረት ስራ ማህበራት መበራከታቸው በተለያዩ ሙያ ሰልጥነው መስራት እየቻሉ የፋይናንስ እጥረት የገጠማቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን በፋይናንስ በማገዝ ወደስራ ከማስገባት አንጻር ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
የዚሁ አንድ አካል የሆነው አስተማማኝ የብድርና ቁጠባ ኃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ስራ ማህበር መመስረቱ በተለይም ዞኑ እምቅ ሀብት ያለው እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት እንደመሆኑ መጠን በአነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩትን በመደገፍ ኢኮኖሚውን ይበልጥ የማነቃቃት ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል። ለዚሁም በርካታ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን በማቀፉ በቅርብ ጊዜ ለውጥ እንደሚያስመዘግብ ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የአስተማማኝ የብድርና ቁጠባ ኃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አቡዱሽ ጎንደር በበኩላቸው ማህበሩ በ20 ሚሊየን ብር ካፒታል እና 645 የማህበሩ አባላት መመስረት መቻሉንም ተናግረዋል።
ማህበሩ አርባ አይነት ቁጠባ እና ከሰባ በላይ የብድር አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቁመው አባሎቹ ሀያ አምስት ከመቶ ቆጥበው ሰባ አምስት ከመቶ ብድር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በተለይም የመስራት አቅም እያላቸው የፋይናንስ እጥረት የገጠማቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጨነቁ ኮንታር በበኩላቸው፤ ማህበሩ በዝቅተኛ ኢኮኖሚ ውስጥ ለሚገኘው የማህበረሰቡ ክፍል የፋይናንስ ችግርን የሚፈታና ተደራሽ የሚያደርግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተለይም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ተሸክሞ የሚገኘውን ሰፊ አርሶ አደርና ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ የፋይናንስ አጋር በመሆን ይሰራል ብለዋል።
በተሟላ ቴክኖሎጂና ዝግጁነት ወደ ስራ መግባቱ አገልግሎቱን ፈጣን፣ ግልጽና አስተማማኝ እንዲሆን ያግዘዋል ያሉት አቶ ጨነቁ በረጅም ጊዜ በቀጠናው ተወዳዳሪና ቀዳሚ ባንክ ለመሆን ያለውን ራዕይ የሚያመላክት ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
የአማን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መስፍን አለማየሁ በበኩላቸው፤ በኮሌጁ በተለያዩ ሙያ እየሰለጠኑ ያሉ እና በተለያዩ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሙያዎች የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ በማህበሩ በመታቀፍ የስራ እድል እንዲመቻችላቸው የጋራ የውል ስምምነት በመፈራረም ከማህበሩ ጋር እንደሚሰሩ ተናግረው ይኸውም ሰልጣኝ ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ በቀጥታ ወደስራ እንዲገቡ ያስችላቸዋልም ብለዋል።
የማህበሩ አባላት የአስተማማኝ የብድርና ቁጠባ ኃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ስራ ማህበር አባል በመሆናቸው በአነስተኛ የገንዘብ ቁጠባ መጠን ብድር ተጠቃሚ ሆነው ወደተሻለ የስራ ዘርፍ ለመሰማራት እንዲችሉ በማመን ወደአባልነቱ መቀላቀላቸውን ጠቁመዋል። በዚህም እራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እንደሚለውጡም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
በስልጤ ልማት ማህበር ለ3ኛ ጊዜ በተዘጋጀው የችግኝ ተከላ መርሀግብር ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር የተሰበሰቡ የአካባቢው ተወላጆች በዞኑ በሚገኙ የላንፉሮ ወረዳና ጦራ ከተማ አስተዳደር ችግኞችን ተክለዋል ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ እና የአደረጃጀት ዘርፍ የ2018 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዕቅድ ዙሪያ በታርጫ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው
በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመረጃ ጥራት ዙሪያ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ