ግብራቸውን በባንክ መክፈላቸው ሊያጋጥም የሚችለውን እንግልት እንዳስቀረላቸው ግብር ከፋዮች ገለጹ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ግብራቸውን በባንክ መክፈላቸው ሊያጋጥም የሚችለውን እንግልት እንዳቀረላቸው በካፋ ዞን የዴቻ ወረዳ ግብር ከፋዮች ተናገሩ።
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የቀን ገቢ ግመታ የመክፈል አቅምን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መከናወኑን ጠቁመዋል።
ግብራቸውን በወቅቱ ሲከፍሉ ያገኘናቸው ግብር ከፋዮች መካከል አቶ አጦ ገብረዮሐንስ፤ አቶ ብርሃኑ ወልደጊዮርጊስ፤ አቶ አስራት ተሰማ እና አቶ ብርሃኑ ወዳጆ በሰጡት አስተያየት ግብር ለአንድ አካባቢ ልማት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
ግብር ሰርተን ካገኘነው ትርፍ የምንከፍለው የውዴታ ግዴታችን ነው ያሉት ግብር ከፋዮቹ፥ በየአመቱ በሚከፍሉት ግብር እንደ ወረዳ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገበ እንደሆነም ገልጸዋል።
የግብር አከፋፈል ስርዓቱ በባንክ መሆኑ የግብር ከፋዮችን እንግልት ከማስቀረቱም ባሻገር ከሰው እጅ ንክኪ በጸዳ መልኩ እንዲከፍሉ ማስቻሉንም ተናግረዋል።
ግብራቸውን በየሩብ አመት መክፈል መቻላቸው ከዚህ ቀደም የአመቱን ግብር አንድ ጊዜ በመክፈል የሚደርስባቸውን ጫና ማቃለሉን ነው የገለጹት።
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የቀን ገቢ ግመታ አቅማቸውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መከናወኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጭዎቹ፥ ግብራቸውን ለመክፈል ሲመጡ ባለሙያዎች በጥሩ ሁኔታ እያስተናገዱ እንደሆነም ተናግረዋል።
የዴቻ ወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላኩ አጥናፉ በበኩላቸው፥ በ2019 በጀት አመት ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት 389 ሚሊዮን 144 ሺህ 500 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
ይሄ መረጃ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከ18 ሚሊዮን 842 ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ጠቁመው፥ የግብር አከፋፈል ሂደትን ከባንክ ጋር በማስተሳሰር የተቀላጠፈ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ከዚህ ቀደም እጅ-በእጅ የሚሰበሰበውን ገቢ በባንክ እንዲከፍሉ በማድረግ ለግብር ከፋዮች ከዕዳ ነጻ ምስክር ወረቀት ወዲያው እየተሰጣቸው ነው ብለዋል።
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የቀን ገቢ ግመታ በአግባቡ ተሰርቶ መጠናቀቁን የጠቆሙት አቶ መላኩ፥ ግመታው የነጋዴዎችን የዕለት ሽያጭ ገቢን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መከናወኑን ገልጸዋል።
ግብር ከፋዮች የተጣለባቸውን ግብር አምነው እንዲከፍሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የግብር መክፈያ ጊዜ እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2018 አመተ ምህረት ድረስ ብቻ መሆኑን ተገንዝበው በወቅቱ በመክፈል ከአላስፈላጊ ቅጣትና እንግልት እንዲተርፉ አቶ መላኩ አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ሀብታሙ ታደሰ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የኮንታ ዞን ም/ቤት 4ኛ ዙር 4ኛ ሥራ ዘመን 26ኛው መደበኛ ጉባኤው ተጠናቀቀ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
አጫጭር የሙያ ክህሎት ስልጠና ማግኛታቸው በሚሰማሩበት የውጭ ሀገራት ሁሉ ተግባራቸውን እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው በሆሳዕና ከተማ የሚገኙ ሰልጣኞች ተናገሩ