አጫጭር የሙያ ክህሎት ስልጠና ማግኛታቸው በሚሰማሩበት የውጭ ሀገራት ሁሉ ተግባራቸውን እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው በሆሳዕና ከተማ የሚገኙ ሰልጣኞች ተናገሩ

አጫጭር የሙያ ክህሎት ስልጠና ማግኛታቸው በሚሰማሩበት የውጭ ሀገራት ሁሉ ተግባራቸውን እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው በሆሳዕና ከተማ የሚገኙ ሰልጣኞች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለውጭ ሀገራት ስራ ስምሪት አጫጭር የሙያ ክህሎት ስልጠና ማግኛታቸው በሚሰማሩበት ሀገር ሁሉ ተግባራቸውን በተገቢው እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ የሚገኙ አንዳንድ ሰልጣኞች ተናገሩ።

የውጭ ሀገራት ስራ ስምሪት አጫጭር የሙያ ክህሎት ስልጠና የሚሰጡ የግል ተቋማት በዘርፉ በመንግስት ላይ የሚፈጠረውን ጫና የሚቀንሱ በመሆናቸው፥ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የሀድያ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ አስታውቋል።

የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አጫጭር የሙያ ስልጠና ዜጎች ስለሚሰማሩበት የስራ መስክ ክህሎት ኖሯቸው የተሰጣቸውን ስራ በብቃት እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።

በሙያ ክህሎት ማነስ ምክንያት በአሰሪዎቻቸው የሚደርሰውን ተጽዕኖ የሚያስቀር በመሆኑ፥ ስልጠናው ከውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ባለፈ ለሀገር ውስጥ የስራ ዕድሎችም ጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተጠቁሟል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ለውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ሙያ ክህሎት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል በአና የሙያ ክህሎት ማሰልጠኛ ተቋም ያነጋገርናቸው ሰልጣኞች እንደተናገሩት፥ በህፃናት እንክብካቤ፣ በቤትና ዕቃ አያያዝ፣ በምግብ ዝግጅት እንዲሁም በመሠረታዊ የቋንቋ ችሎታ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

በተቋሙ በቤታቸው የማያውቋቸው እና ዘመናዊ የስልጠና ግብኣቶች መኖራቸውን ገልፀው፥ በዚህ መሰልጠናቸው በሚሰማሩበት ሁሉ ተግባራቸውን በተገቢው እንዲወጡ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የተቋሙ አሰልጣኝ ወርቅነሽ ደመቀ በበኩሏ በማሰልጠኛ ተቋሙ የሚገኙ የስልጠና ግብአቶች የውጭ ሀገር ስታንዳርድ ያሟሉ መሆናቸውን ገልጻለች።

የማሰልጠኛ ተቋሙ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰላማዊት ደምሴ በበኩላቸው ሰልጣኞች በቂ የሙያ ክህሎት እንዲኖራቸው በሁሉም ዘርፍ በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

ተቋሙ ስራ ከጀመረበት ከአንድ አመት ወዲህ በበቂ ግብአት ዜጎችን በሙያ እያበቃ መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ ሰላማዊት፥ ሰልጣኞቹ ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ የክልሉ ትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤት ብቃታቸውን በመመዘን ሰርቲፍኬት እንደሚያገኙም ተናግረዋል።

በዚህ ዙር 180 ሠልጣኞች ለብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል።

በሀድያ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ የተቋማት አቅም ግንባታና ጥራት ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ተክሌ ፊታሞ እንደገለፁት፥ በዞኑ ለውጭ ሀገር ስራ ስምሪት የሙያ ስልጠና የሚሰጡ 24 የመንግስትና የግል ተቋማት መኖራቸውን ጠቁመው፥ ስልጠናው ከሆቴል አስተዳደር ጋር የሚያያዝ ሲሆን ከውጭ ሀገር ስራ ስምሪትን እና መደበኛ ገበያ ተኮር ስልጠና ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።

የማሰልጠኛ ተቋማቱን የስልጠና ሂደት ዞኑ ክትትል እንደሚያደርግ የገለፁት አቶ ተክሌ፥ በግል እየሰሩ ያሉ ተቋማት በዘርፉ በመንግስት ላይ የሚፈጠረውን ጫና እንደሚቀንሱም ተናግረዋል።

ስልጠናው የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት የሚሄዱ ዜጎች ባገኙት የሙያ ክህሎት ስራቸውን በዕወቀት እንዲሰሩ ከማገዙም ባለፈ ለሀገር ውስጥ የስራ ዕድሎችም ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳህና ጣቢያችን