የማዕድን ሀብቶችን ከህገ ወጥ ደላላና የኮንትሮባንድ ንግድ ለመግታት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

የማዕድን ሀብቶችን ከህገ ወጥ ደላላና የኮንትሮባንድ ንግድ ለመግታት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕድን ሀብቶች ከህገ ወጥ ደላላና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመግታት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ማዕድን እና ኢነርጂ ኢጀንሲ አስታወቀ።

በክልሉ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት አመት 348 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ መላክ መቻሉ ተመላክቷል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተለያዩ የማዕድን ሀብት ፀጋዎች ያሉት ክልል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፥ በከበሩ ማዕድናት ወርቅ፣ በእንዱስትሪ ልማት፣ በድንጋይ ከሰል እና በኮንስትራክሽን ማዕድናት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ማዕድን እና ኢነርጂ ኢጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ውልያብ ተናግረዋል።

ክልሉ በአሁኑ ወቅት በዋናነት የወርቅ ማዕድን ስራ ምርትን ወደ ብሄራዊ ባንክ ለመላክ በርካታ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ኃላፊው፥ የገበያ ሥርዓቱን በማዘመን እና ሕገ ወጥ አሠራሮችን ወደ ህጋዊ ስርዓቱ ማስገባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከማዕድን ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በተለይ ከዞኖች አስተዳደር፣ ከወረዳና ቀበሌ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የተለያዩ ድጋፍ እና ክትትል ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል።

ይህም ዘርፉ ምን ያህል አቅም እንዳለው እና ትክክለኛ አሠራር ሲዘረጋ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደሚችል ያረጋገጠ ክስተት እንደሆነም ተናግረዋል።

ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች የልማቱ ተጠቃሚ መሆን መቻሉ ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን እና አሁን ላይ የአካባቢው ማኅበረሰቦች የሮያሊቲ ክፍያ እና ታክስን በተሻለ ሁኔታ እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል ብለዋል።

ይህም በአካባቢው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ የማዕድን ማውጣት ሥራዎቹ የተፈጥሮ ሚዛንን በማይጎዳ መልኩ እንዲካሄዱም የቁጥጥር ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

እነዚህ ጅምሮች ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ መሠረት የጣሉ በመሆናቸው በቀጣይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነት ባላቸው ማዕድናት ላይ ሰፊ ጥናት እና ምርምር በማድረግ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ለማዋል መታቀዱን አሳስበዋል።

በክልሉ በተጠናቀቀው በ2018 በጀት አመት 348 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ መላክ መቻሉንም ዶክተር ጌታቸው ገልፀዋል።

በአጠቃላይ የታዩት እነዚህ ለውጦች፣ የማዕድን ዘርፉ ከሕገ ወጥነት ፀድቶ የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ሊደግፍ በሚችልበት ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን የሚያሳዩ በመሆናቸው በቀጣይ ጉድለቶችን በማረም ጠንካራ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን ዳጉሳ – ከሚዛን ጣቢያችን