በትራንስፖርትና መንገድ ልማት ዙሪያ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
በሸካ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ በ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርትና በ2019 ጠቋሚ ዕቅድ ዙሪያ በቴፒ ከተማ መክሯል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የሸካ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ በላቸው ጋራ፤ የትራንስፖርትና መንገድ ስራ በ2018 ዓ.ም በነበረው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት የህብረተሰቡ ዋነኛ ጥያቄ ስለነበር የሚመለከተው አካል በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በዚህም በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚገነቡ የተለያዩ መንገዶችን በሁሉም መዋቅር አጠናክሮ ማስቀጠል ከሁሉም እንደሚጠበቅና በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ያሉትን አላስፈላጊ የታሪፍ ጭማሪዎችን ለመከላከል መስራት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
የሸካ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ሃራ በወቅቱ እንደገለፁት፤ በ2018 በጀት ዓመት የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል ለቀጣይ በጀት አመት የሚታዩ ክፍተቶችን በማረምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በቅንጅት በመቅረፍ ይሠራል ብለዋል።
በትራንስፖርት ዘርፍ ያሉትን የስነ-ምግባርም ሆነ ሌሎች ችግሮችን በመቅረፍ በመንገድ ዘርፍም ህብረተሰቡን በማስተባበር ቀጣይነት ባለው ሂደት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በመድረኩ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ደህንነት ማረጋገጫ ቡድን አስተባባሪ አቶ መላኩ ደሰኖ፤ የሪፎርም ስራዎች፣ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችና አሽከርካሪዎችን ማሰማራት፣ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ፣ በትራፊክ አደጋ ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት፣ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተለያዩ መንገዶችን የመገንባቱ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በመንገድ ስራ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ክትትልና ድጋፍ ከማድረግ አኳያ እየተሰራ ያለውን በማጠናከር የሚታዩ ክፍተቶችን በቅንጅት ማረም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የትራንፖርት ዘርፉ ችግር በተለይ የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ ወቅታዊ ብቻ ባለማድረግ ማስፈፀም ይገባል ብለዋል።
ለተነሱ ሀሳብና አስተያየቶች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ እና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ: ምንታምር አስፋው – ከማሻ ጣቢያችን

More Stories
የኮንታ ዞን ም/ቤት 4ኛ ዙር 4ኛ ሥራ ዘመን 26ኛው መደበኛ ጉባኤው ተጠናቀቀ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
አጫጭር የሙያ ክህሎት ስልጠና ማግኛታቸው በሚሰማሩበት የውጭ ሀገራት ሁሉ ተግባራቸውን እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው በሆሳዕና ከተማ የሚገኙ ሰልጣኞች ተናገሩ