“ማሬስካም ቢሆን እንደ ፔፕ ድንቅ ነው” ሚኬል አርቴታ
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከኮምዩኒቲ ሺልድ ጨዋታ በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ማንቸስተር ሲቲን ለ10 ዓመታት መርተው የለቀቁትን ፔፕ ጋርዲዮላን ተክተው የአሰልጣኝነት መንበሩን የተረከቡትን ኤንዞ ማሬስካን አሞግሷል።
አርቴታ ለጋርዲዮላ ያለውን ጥልቅ አክብሮት ከመግለጹ ባሻገር፣ በቀድሞ የስራ ባልደረባው ማሬስካ አቅም ላይ ሙሉ እምነት እንዳለው ተናግሯል።
አርቴታ ለጋርዲዮላ በሲቲ ለነበረው አስደናቂ የስኬት ዘመንና ለእንግሊዝ እግር ኳስ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ሲናገር”ለጋርዲዮላ ያደረገውን ነገር ለማመስገን እና ለማሞገስ ቃላት ያጥሩኛል። ለፕሪምየር ሊጉ እና ለሀገሪቱ እግር ኳስ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው” ያለ ሲሆን “ጨዋታውን የምንረዳበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። እግር ኳሱን ቀደም ሲል አይተነው ወደማናውቀው ከፍተኛ የጥራት ደረጃ እና መለኪያ አሸጋግሮታል” ሲል ተናግሯል።
አርቴታ አክሎም”ፔፕ ድንቅ፣ ልዩ እና በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ምርጡ አሰልጣኝ ነው። በፕሪምየር ሊጉ ውስጥ በጣም የሚናፈቅ ይመስለኛል ምንም እንኳን አሰልጣኞች ያን ያህል ባይናፍቁትም! ከእሱ ጋር ላሳለፍኩት ጊዜ ከልብ የመነጨ ምስጋና አለኝ። ሁሉንም አሰልጣኞች እና ቡድኖች በተለየ መንገድ እንዲሰሩ እና እንዲያስቡ አድርጓል፤ ከእሱ ጋር መስራት ደስ የሚል ነበር” ብሏል።
ኤንዞ ማሬስካ የጋርዲዮላን ቦታ ተክተው የማንቸስተር ሲቲ ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ፣ አርቴታ ሲቲ በጥሩ እጅ ላይ መውደቁን ገልጿል።
“አሁን የኤንዞ ጊዜ ነው” ያለው አርቴታ “እሱን በደንብ ስለማውቀው እንደ ፔፕ ሁሉ ድንቅ እና ጎበዝ አሰልጣኝ ነው፤ ለክለቡም የተለየ እና አዲስ ነገር እንደሚያቀርብ አልጠራጠርም” ብሏል።
ፔፕ ጋርዲዮላ ከ10 ዓመታት ስኬታማ የሲቲ ቆይታ በኋላ ከክለቡ ሲሰናበቱ፣ የቀድሞው የሲቲ ረዳት አሰልጣኝ እና የቼልሲው አሰልጣኝ የነበሩት ኤንዞ ማሬስካ የሲቲ አዲሱ ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸው ይታወቃል።
ሚኬል አርቴታ እና ኤንዞ ማሬስካ ሁለቱም በማንቸስተር ሲቲ ውስጥ በፔፕ ጋርዲዮላ ስር በረዳት አሰልጣኝነት አብረው የሰሩ በመሆናቸው፣ የእርስ በእርስ አቅማቸውንና የጋርዲዮላን የእግር ኳስ ፍልስፍና በቅርበት የሚያውቁ ናቸው።
አዲሱ የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ በመጀመሪያው ይፋዊ ጨዋታቸው በኮምዩኒቲ ሺልድ ፍፃሜ ከሚኬል አርቴታው አርሰናል ጋር ይገጥማሉ።
ጨዋታው የፊታችን ዕሁድ በካርዲፍ ሚሊኒየም ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ
“ማሬስካም ቢሆን እንደ ፔፕ ድንቅ ነው” ሚኬል አርቴታ

More Stories
የፒኤስጂው ኮከብ ኪቪቻ ክቫራትስኬሊያ አዲስ ወኪል መረጠ!
የክረምት እግር ኳስ ሻምፒዮናው የተሻለ አቅም ያላቸው ተተኪ ስፖርተኞችን የምናፈራበት ነው – የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር
ቼልሲ ኤንዞ ፈርናንዴዝን ለመሸጥ ቀነ ገደብ አስቀመጠ