የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎትና ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሚስዮኖች ጋር በመተባበር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበረከተ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎትና ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሚስዮኖች ጋር በመተባበር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበረከተ

ድጋፉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በጋጮ ባባ ወረዳ በጎርፍና በመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች እየተገነባ ያለውን የመኖሪያ መንደር በፍጥነት ለማጠናቀቅ ያለመ ነው።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በተለያዩ ጊዜያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ እያበረከተ መቆየቱን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት በጋሞ ዞን በደረሰው አደጋ የመልካምነት አሻራ እያሳረፈ እንደሆነ ገልፀዋል።

ድጋፉ በአደጋው ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች የተሻለ እና ዘላቂ የኑሮ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነና ተፈናቃዮችን ወደ መደበኛ ኑሮ ለመመለስ ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአደጋ ጊዜ የተጎዱ ዜጎችን በጊዜያዊ መጠለያ ብቻ ሳይሆን በቋሚ መኖሪያ ማቋቋም የተጎጂዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሃድሶ ለማፋጠን እንደሚረዳም ተጠቁሟል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ(ዶ/ር) በዚህ ዓመት በመጋቢት ወር በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ 1300 የቤተሰብ አባላት ለመደገፍ ከፍተኛ ድጋፍ እየተበረከተ መቆየቱን ገልፀው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላበረከተው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ተጎጂዎች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አጥናፉ ዲዶ የሁሉም ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች አካላት አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት አፈፃፀሙ 60 ከመቶ መድረሱን ገልፀው፤ እስከ ዘመን መለወጫ ለመጀመሪዎቹ 100 ተጎጂ ወገኖች እየተገነባ ያለው ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ብለዋል።

ዘጋቢ: ተነሳ ተረፈ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን