ኦሞ ባንክ ሳውላ ዲስትሪክት በ2018 በጀት ዓመት ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ቁጠባ ማስመዝገቡን ገለጸ
“ልዩ ትኩረት ለጋራ ስኬት” በሚል መሪ ቃል ኦሞ ባንክ ሳውላ ዲስትሪክት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 ዕቅድ ዙሪያ የውይይት መድረክ በሳውላ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ፤ ባንኩ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኢኮኖሚ ለማሻሻል የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
የኦሞ ባንክ ሳውላ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድማገኝ ዘነበ በበኩላቸው፤ በዲስትሪክቱ ሥር የሚገኙ 10 ቅርንጫፎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ተወዳዳሪነቱን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በተከናወነው ሥራ ባንኩ ከ20 ሺህ 735 በላይ አዳዲስ የብድር ደንበኞችን በማፍራት ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ቁጠባ ሰብስቧል።
በተጨማሪም ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር በማስመለስ ከ168 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ማሰራጨቱን አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል።
የሳውላ ዲስትሪክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀይሉ ደምሴ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን ለተሳታፊዎች አቅርበው በእቅዱ ላይ ውይይት ተደርጓል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ኦሞ ባንክ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ አቅምና የቁጠባ ባህል በማሳደግ፣ በተለይም ለሴቶች በተመጣጣኝ ወለድ የተሻለ የብድር አማራጭ በማቅረብ ውጤታማ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
በመድረኩ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች የእውቅና መርሃ ግብርም ተካሂዷል።
ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ እና የአደረጃጀት ዘርፍ የ2018 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዕቅድ ዙሪያ በታርጫ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው
እየተካሔደ ያለው ሀገራዊ ምክክር በሀገሪቱ አንድነት እና ሠላም ለማስፈን ፋይዳው የጎላ መሆኑን የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ
የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎች በዘላቂነት እንዲመለሱ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኧሌ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ገለፀ