ቼልሲ ኤንዞ ፈርናንዴዝን ለመሸጥ ቀነ ገደብ አስቀመጠ

ማንቸስተር ሲቲ አርጀንቲናዊውን አማካይ ኤንዞ ፈርናንዴዝን ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየቱን ተከተሎ፣ ቼልሲ ድርድሩን ለማጠናቀቅ እስከ አርብ አመሻሽ 11:00 ድረስ የጊዜ ገደብ አስቀምጧል።

ቼልሲ የ23 ዓመቱን አማካይ ዋጋ 120 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣበት ሲሆን፣ ማንቸስተር ሲቲ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በፊት የቀረበውን የዋጋ ጥያቄ ካላሟላ ተጫዋቹን አሁን ባለው የዝውውር መስኮት የመሸጥ ፍላጎት የለውም።

ፈርናንዴዝ በስታምፎርድ ብሪጅ የ6 ዓመታት ረጅም ኮንትራት የሚቀረው ቢሆንም፣ ከቀድሞው የቼልሲ አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ጋር የነበረው ጠንካራ ግንኙነት ወደ ኢትሃድ የመዛወር እድሉን አጎልቶታል።

የማንቸስተር ሲቲ ለኤንዞ ፈርናንዴዝ ትኩረት መስጠት ከባርሴሎና የዝውውር እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው።

ባርሴሎና ስፔናዊውን አማካይ ሮድሪ ለማስፈረም ያቀረበው የ40 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ በሲቲ ውድቅ ቢደረግም፣ ካታላኖቹ አሁንም ተጫዋቹን ለማስፈረም ጥረት በማድረጋቸው ሲቲዎች ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ተገደዋል።

በተጨማሪም ማንቸስተር ሲቲ ከሊሉ ወጣት አማካይ አዩብ ቡአዲ ጋር ድርድር በማድረግ ላይ ይገኛል።

ኤንዞ ፈርናንዴዝ ባለፈው ሚያዚያ ወር “በማድሪድ መኖር ደስ ይለኛል” የሚል አስተያየት መስጠቱን ተከተሎ ለሁለት ጨዋታዎች ከስብስቡ ውጪ ተደርጎ ነበር።

ምንም እንኳን ተጫዋቹ እና ወኪሉ ለሰጡት አስተያየት ይቅርታ ጠይቀው የኮንትራት ማሻሻያ ቢጠይቁም፣እስካሁን ድረስ ውሉ አልታደሰም።

ሪያል ማድሪድ ግን ተጫዋቹን የማስፈረም ፍላጎት እንደሌለው ይፋዊ መግለጫ አውጥቷል።

በፈረንጆቹ ጥር 2023 ከቤንፊካ በ107 ሚሊዮን ፓውንድ ቼልሲን የተቀላቀለው ፈርናንዴዝ፣ የወደፊት እጣ ፈንታው እስከ አርብ በሚደረጉ ውይይቶች ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ