ለትምህርት ሥራ ስኬታማነት ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነትና በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት የዳውሮ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2019 የትምህርት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ “የጋራ ትጋት ለትምህርት ልማት እምርታ” በሚል መሪ ቃል በታርጫ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ፤ የዘመኑን የትምህርት ስራ ለማሻሻል “የጋራ ትጋት ለትምህርት ልማት እምርታ” በሚል መሪ ቃል የንቅናቄ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አንስተው በዚህም ባለፈው ትምህርት ዘመን የታዩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠልና ጉድለቶችን በመቅረፍ ለበለጠ ውጤታማነት በጋራ መትጋት ይገባል ብለዋል።
የትምህርት ግብአት ከማድረስ አኳያ ያለው መንጠባጠብ፣ በምግብ ፕሮግራም ተማሪዎችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ የታዩ ክፍተቶችን በመቅረፍ ለቀጣይ ዓመት ያለ መንጠባጠብ በመስራት የተማሪ ውጤትን ለማሻሻል እንዲሰራም አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ እጩ ዶ/ር ታማኝ ሀይሌ፤ የትምህርት ዘርፍ ውጤታማነት ለሁለንተናዊ ብልፅግና መሠረት መሆኑን ገልፀው በሀገራችን ይህንን ለማጠናከር የተለያዩ የትምህርት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተቀርፀው እየተተገበሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዞኑ ይህንን በማጠናከር በ2018 ትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማራቸውን አንስተው በዞኑ ለሁለተኛ ጊዜ ከ1 ሺህ 2 መቶ በላይ ተማሪዎችን በበይነ መረብ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ማስፈተን መቻሉን አስረድተዋል።
በ2019 ትምህርት ዘመን ከ2 መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ግብ ተጥሎ ንቅናቄ መጀመሩን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ለዚህም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራዎች ትኩረት እንዲደረግባቸው አመላክተዋል።
ለ2019 ትምህርት ዘመን በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ ህብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳተፍ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደሚያከናውኑ የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
በመድረኩ የ2018 የትምህርት ልማት ስራዎች አፈፃፀምና የ2019 ዕቅድ ቀርቦ ውይይት የተደረግ ሲሆን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ዳዊት ሚኖታን ጨምሮ ሌሎች የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የትምህርት ሴክተር አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ አንዱዓለም ኡማ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
በበጀት አመቱ በ71 ሺህ 219 መዛግብት ላይ ውሳኔ መስጠት መቻሉ ተገለጸ
የጉራጌ ማህበረሰብ ባህላዊ እሴቶች ሳይበረዙ ለትውልድ ለማስተላለፍ የኪነ ጥበብ ዘርፉን በማጠናከር ላይ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት 67 ቢሊየን ብር በጀት አጸደቀ