የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተቋሙ ሰራተኞች በአደረጉት ጥረት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚዛን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ

የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተቋሙ ሰራተኞች በአደረጉት ጥረት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚዛን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

ጽህፈት ቤቱ በ5 የብሄረሰብ ቋንቋዎች ለ16 ዓመታት ባህልና ወግ እንዲሁም እሴቶችን በጠበቀ መልኩ ለአድማጭ ተመልካቾች ዜና እና ፕሮግራም ሳቢ በሆነ መንገድ ሲያቀርብ የቆየ መሆኑ ተመላክቷል።

ተቋሙም እነዚህን ሁሉ አመታት ተሻግሮ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2019 በጀት አመት ዕቅድ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ትዕዛዙ ኬንጫ እንደተናገሩት፤ የሚዛን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እንደ ሚዲያ ተቋም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ መረጃዎችን በአምስት የብሄረሰብ ቋንቋዎች የህረተሰቡን ባህል እና ኪነጥበብ እንዲሁም ሀገራዊ እና ክልላዊ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ዘገባዎችን በመስራት ለአድማጭ ተመልካቾች እያደረሰ የሚገኝ ነው።

በቀጣይ 2019 በጀት አመት በይዘት ዘርፍ የተሻለ አፈፃፀም ለማምጣት ከባለድርሻ አካላት እና ፈፃሚ ጋዜጠኞች ጋር መግባባት መፍጠር መቻሉንም ገልፀዋል።

በ2018 በጀት አመት እንደተቋም ችግር የነበረው በማሰራጫ ጣቢያ የሚገኘው የማሽን ዕቃዎች ብልሽት ተግዳሮት የነበረ ሲሆን በቀጣይ ክልሉ እና ዞኑ በመቀናጀት ችግሮችን መፍታት የሚችሉበት መግባባት ላይ መድረሳቸውን አውስተዋል።

የተቋሙ ሰራተኞች በበጀት አመቱ የነበሩባቸውን ክፍተቶች በማረም በ2019 ከፍተኛ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የተጣለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች እንደተቋም የተሰሩ ስራዎች የህብረተሰቡን ባህል እና ወግ ጠብቀው የተዘጋጁ ዜናዎች እና ፕሮግራሞች እንዲሁም በሚዲያ ቴክኖሎጂ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ ሀሳብ አስተያየት ከሰጡን መካከል የተቋሙ ሬዲዮ ኬዝ አስተባባሪ አቶ ነብዩ መካሻ እንደተናገሩት፤ የተቋሙን አሰራር ለማሻሻል ጥምረት በመፍጠር የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል።

በተቋሙ የቴሌቪዥን ኬዝ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዮት በቀለ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ በ2018 በጀት ዓመት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ሰፊ ሽፋን መሰጠቱን ጠቁመው፤ ሌሎች ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮችም ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ የዘንድሮው የተቋሙ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑን ገልፀው የተመዘገቡትን ውጤቶች ለማስቀጠል የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚያስፈልግ፣ የሬዲዮ የተደራሽነት ክፍተት መስተካከል እንዳለበት፣ የሰው ኃይልና የግብአት ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች ከሚለከታቸው የዘርፉ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ በማፅደቅ መድረኩ ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን ዳጉሳ – ከሚዛን ጣቢያችን