ኒውካስል ዩናይትድ ብሩኖ ጊማሬሽን በ75 ሚሊዮን ፓውንድ ለአርሰናል ለመሸጥ ተስማማ



የእንግሊዙ ክለብ ኒውካስል ዩናይትድ ብራዚላዊውን አማካኝ ብሩኖ ጊማሬሽን በ75 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ለሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል አሳልፎ ለመስጠት ከስምምነት መድረሱ ተገልጿል።

አርሰናል ዝቅተኛ የዝውውር ሂሳብ በማቅረብ ድርድሩን ቢጀምርም፣ ኒውካስል በበኩሉ ከፍ ያለ ዋጋ ይፈልግ ነበር።

ይሁን እንጂ ሁለቱ ክለቦች በ75 ሚሊዮን ፓውንድ መስማማታቸው የ28 ዓመቱ አማካኝ ወደ አርሰናል ለመዛወር የነበረውን ፍላጎት ለማሳካት መንገድ ከፍቶለታል።

ከዚህ ዝውውር የጊማሬሽ የቀድሞ ክለብ ሊዮን የ20 በመቶ የትርፍ ድርሻ ስላለው ከ6 እስከ 7 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያገኝ ይሆናል።

ጊማሬሽ በስፔን ከኒውካስል ጋር በቅድመ-ውድድር ዘመን ዝግጅት ላይ የነበረ ቢሆንም፣ የፕሪሚየር ሊጉን ሻምፒዮን አርሰናልን ለመቀላቀል የሕክምና ምርመራ ለማድረግ ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

ተጫዋቹ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ለኒውካስል፤ ክለቡን ለቆ ወደ አርሰናል የማሸጋገር ፍላጎት እንዳለው አስታውቆ ነበር።

በ2023 የአምስት ዓመታት ኮንትራት ፈርሞ የነበረው ጊማሬሽ፣ ሁለት ዓመታት የቀሩት ቢሆንም በውሉ ላይ ተካቶ የነበረው የ100 ሚሊዮን ፓውንድ የውል ማፍረሻ ጊዜው በማልፉ ክለቦቹ በድርድር ሂሳቡን እንዲቀንሱት ሆኗል።

ጊማሬሽ በ2022 ሊዮንን ለቆ ኒውካስልን ከተቀላቀለ ወዲህ በ153 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 30 ግቦችን በማስቆጠር እና 26 ግቦች እንዲቆጠሩ አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን የ2025 የካራባኦ ካፕ ዋንጫን ከክለቡ ጋር ማንሳት ችሏል።

በቅርቡ በተጠናቀቀው የ2026 ዓለም ዋንጫም ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን በሁሉም 5 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 4 ግብ የሆኑ የመጨረሻ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ