የ2018 ዓ.ም የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዲላ ክለስተር የችግኞች ተከላ እየተካሄደ ነው

የ2018 ዓ.ም የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዲላ ክለስተር የችግኞች ተከላ እየተካሄደ ነው


በመርሃ ግብሩም ከ69 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አሳውቋል።


መርሃ ግብሩ በጌዴኦ ዞን በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ከማለዳው 12 ሰዓት ላይ በይፋ ተጀምሯል፡፡


መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አሰተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) እንደገለጹት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ እንደ ሀገር በአንድ ጀምበር ለመትከል የተያዘው የ800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ አካል መሆኑን ገልፀዋል።


በክልሉ በተመረጡ አካባቢዎች 69 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት ኃላፊው አሰቀድሞ በተሰራው የቅድመ ዝግጅት ስራም ከእቅድ በላይ እንደሚከናወን ነው የተናገሩት።


በአንድ ጀንበር ለመትከል በተያዘው የ69 ሚሊዮን ችግኝ ተከላም 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን አርሶ እና አርብቶ አደር እንዲሁም የከተሜው ህዝብ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልፀዋል።


በዘንድሮው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትኩረት የተደረገባቸው የፍራፍሬ፣ የቡና እና የእንሰት ችግኞች መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር መሪሁን ይህም በአርሶ አደሩ ማሳ እና በ1384 ተፋሰስ በ28 ሺህ 900 ሄክታር ላይ የሚከናወን መሆኑን ነው የገለጹት።


የደን ወይም የጥምር ዛፎች ተከላም በተጓዳኝ በወል መሬቶች ላይ አየተተከለ እንደሚገኝም አያይዘው አስረድተዋል።


በክልሉ በበልግ ወቅት በሚያዝያ ወር 180 ሚሊዮን እንዲሁም በሐምሌ ወርና ክረምት ወቅት 324 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።


በአንድ ጀምበር ከሚተከሉት 69 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 38 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞች በዲጂታል የሚመዘገብ ሲሆን ቀሪው 31 ሚሊዮን ችግኝ ደግሞ በኮማንድ ፖስት ሪፓርት የሚመዘገብ ይሆናል ብለዋል።


በዘንድሮው ዓመት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ የዝናብ እጥረት መከሰቱን ገልጸው ህዝቡ የተተከሉ ችግኞችን ውሃ በማጠጣትና በመንከባከብ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።


ዘጋቢ:- ደረሰ አስፋው