በኣሪ ዞን በ1 ጀንበር 4.9 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል
ተስፋን እንትከል በሚል መርህ ዘመቻው በደቡብ ኣሪ ወረዳ ጎመር ቀበሌ በይፋ ተጀመረ ሲሆን የወረዳው ነዋሪዎችም በነቂስ ወጥተው በመሳተፍ ላይ ናቸው።
እንደ ሀገር የተጀመረው የ1 ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዘንድሮው የ2018 ዓ.ም. መርሃ ግብር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ ተቀምጦለታል።
4.9 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ድርሻውን የተቀበለው የኣሪ ዞንም ይህንኑ ከግብ ለማድረስ በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቆ የማስጀመሪያ መርሃ ግብሩን በደቡብ ኣሪ ዞን ጎመር ቀበሌ አካሂዷል።
በወቅቱ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኣሪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ገብሬ ባይስማይ እንደ ወረዳ 1.6 ችግኝ ለመትከል ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ የማሳደግ ኃላፊነትም የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ተስፈን እንተክላለን በሚል መርህ በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ሲሆን በአረንጓዴው የጎመር ቀበሌ መከናወኑ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል።
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የተጀመረው ዘመቻ በሁሉም አካባቢዎች መትከላችን የነገ ስራችንን ዛሬ አስቀድመን በማጠናቀቅ የተሻለ ነገን ዕውን ለማድረግ ኃላፊነታችንን የምንወጣበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በተለያዩ ምክንያት የተመናመኑ ችግኞችን ለመመለስም በኣሪ ዞን በአጠቃላይ ከ4.9 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደሚተከል በመጠቆም የሚተከሉ ችግኞችም የአካባቢን ስነ ምህዳር በመጠበቅ ረገድ ጉልህ ፋይዳ ይኖራቸዋል፤ ስለዚህም መንከባከብ ይጠይቃል ብለዋል።
የምንተክላቸው ችግኞች እንደ ህጻናት በክብካቤ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅሰው ወቅቱ ጸሐይ በመሆኑ ይበልጥ መንከባከብ ይገባል ብለዋል።
መርሃ ግብሩ በዋናነት ሶስት አበይት አላማዎችን ለማሳካት ያለመ መሆኑን ጠቅሰው፤ አካባቢን ከመራቆት የመታደግ፤ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ሞርታማነትን ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል።
በአንድ ጀንበር በክልሉ 69 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ የጠቀሱት ኃላፊው በዕለቱ 800 ሚሊዮን፤ አጠቃላይ በክረምቱ ደግሞ 8 ቢሊዮን ችግኞች እንደ ሀገር የሚተከሉ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ዘመቻው ላይ የተገኙ ሁሉም ዜጎችም 25 ችግኞችን በነፍስ ወከፍ መትከልና በቀጣይም የመንከባከብ አደራውን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
እንደ ሀገር ”በጋራ ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ-ግብር በሸካ ዞን በማሻ ማረሚያ ተቋም ተካሄደ
ችግኝ መትከል ጥሪት ለትውልድ የማስቀመጥ ተግባር በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ ገለፁ።
በሀዋሳ ከተማም ከ220 ሺህ በላይ ችግኞችን በ8ቱም ክፍለ ከተሞች ”ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል”እየተከለች ነው።