በጎፋ ዞን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ዞናዊ መርሃ ግብር በመሎ ኮዛ ወረዳ ማይዘሎ ቀበሌ በይፋ ተጀምሮ በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተካሄደ ነው

በጎፋ ዞን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ዞናዊ መርሃ ግብር በመሎ ኮዛ ወረዳ ማይዘሎ ቀበሌ በይፋ ተጀምሮ በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተካሄደ ነው

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ታደሰ የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ መንከባከብ፣ ከእንስሳትና ከሰው ጉዳት መጠበቅ እና ቀጣይነት ያለው ክትትል ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን በማሳሰብ “ዛሬ የምንተክለው ችግኝ ለልጆቻችን አረንጓዴና ጤናማ አካባቢ ለማውረስ ወሳኝ መሠረት ነው” ብለዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞች የመልክአ ምድሩን ገጽታ በመቀየር ለምግብ ዋስትና፣ ለአፈርና የውኃ ሀብት ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም እና ለግብርና ምርታማነት ማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ የሚገኙ መንግስታዊና የግል ተቋማት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በመርሃ ግብሩ በንቃት እየተሳተፉ ነው።

የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ እንደገለጹት፤ በመርሃ ግብሩ ከ8.4 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በ3,382.9 ሄክታር መሬት ላይ እየተተከሉ ነው።

ከሚተከሉት መካከል ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው የደን ችግኞችና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚገኙባቸው ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በተከታታይ በተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብሮች ምክንያት በዞኑ ከ81 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በደን ተሸፍኗል፤ የደን ሽፋኑም ከ17.2 በመቶ ወደ 21.4 በመቶ ከፍ ብሏል።

የመሎ ኮዛ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉነህ አውሳቶ በተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብሮች ምክንያት የአየር ጸባይ እየተሻሻለ መምጣቱንና ቀደም ሲል የደረቁ የውኃ ምንጮች እንደገና መፍለቅ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

ነዋሪዎችም የተተከሉ ችግኞችን ለመንከባከብ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተከላ መርሃ ግብሩ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች የወረዳው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን