ተቋማቱ በቅንጅት በመስራታቸው የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገቡ እንደሆነ ተገለፀ

ተቋማቱ በቅንጅት በመስራታቸው የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገቡ እንደሆነ ተገለፀ

በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የማሻ ቅርንጫፍ እና የሸካ ማህበረሰብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀፈምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ በማሻ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የማሻ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ታምሩ ጎዱ እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ በሠራተኞች ቅንጅታዊ አሰራር የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል።

ወቅቱ የሚጠይቀውን የሚዲያ አሠራርና ሥነ-ምግባር በመላበስ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለቀጣይ ማስመዝገብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ዘርፍ የአየር ሰዓት በመጨመር የአድማጭ ተመልካቹ ፍላጎት እየተሟላ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የማሻ ቅርንጫፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የይዘት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታደሰ ጋረፎ፤ በበጀት ዓመቱ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ዘርፍ የተሻለ ውጤት የተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የዘርፉ ባለሙያዎች የልፋት ውጤት እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በይዘት ዘርፍ በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ለአድማጭ ተመልካቾች በሶስት ቋንቋዎች መረጃ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የተቋማቱ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት አንፃር ሲታይ የተሻለ መሆኑን ገልፀው የተመዘገቡትን ውጤቶች ለማስቀጠል የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚያስፈልግና የሬዲዮ ተደራሽነት ክፍተት መስተካከል እንዳለበት ተናግረዋል።

ለተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች ከሚለከታቸው የየዘርፉ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ በማፅደቅ መድረኩ ተጠናቋል።

ዘጋቢ: ምንታምር አስፋው – ከማሻ ጣቢያችን