ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መንስኤ በመለየት ችግር ፈቺ መፍትሄዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መንስኤ በመለየት ችግር ፈቺ መፍትሄዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ

የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ ከዞኑ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ጋር በመተባበር፣ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ብላቴ እንደገለጹት፤ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በዘላቂነት ለመቀነስ የችግሮቹን መንስኤ በመለየት ችግር ፈቺ መፍትሄዎችን በልዩ ትኩረት መተግበር ያስፈልጋል።

በተጨማሪም የማህበረሰብ ግንዛቤን ማሳደግ፣ የተቋማትን ቅንጅት ማጠናከርና የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከፖሊስ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ያሉ የፍትህ ተቋማት ለተጎጂዎች ፈጣንና ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የጀመሯቸው ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዞኑ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ጸጋነሽ እንግዳ በበኩላቸው፤ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በቤተሰብ አባላት፣ በአሳዳጊዎችና በወላጆች ጭምር መፈጸማቸው ችግሩን ውስብስብ እያደረገው መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ጥቃቶቹ በተጎጂዎች ላይ የጤና፣ የሥነ ልቦናና የማህበራዊ ችግሮችን በማስከተል ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ማጠናከር እንዲሁም ወንጀለኞችንና ተባባሪዎቻቸውን ለህግ በማቅረብ ማህበረሰቡ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በዞኑ ፍትህ መምሪያ የሴቶችና ህጻናት ልዩ ምርመራና ክስ ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተፈሪ ትርፌ በበኩላቸው፤ በተለይም ለአዕምሮ ህመምና ለአካል ጉዳት የተጋለጡ ሴቶችና ህጻናት ለጥቃት ይበልጥ ተጋላጭ በመሆናቸው ተቋማት በቅንጅት በመስራት ፈጣንና ተገቢ ምላሽ እንዲሰጡ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመድረኩ ችግር ፈቺ መፍትሄዎችን ማስቀመጥ፣ በአንድ ማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ መደገፍና የመረጃ ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለተጎጂዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የቃል ኪዳን ሰነድ በመፈራረም ተጠናቋል።

ተሳታፊዎች ፆታን መሠረት ያደረገ ማንኛውም ጥቃት የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅንጅት ከመከላከል ባሻገር ለተጎጂዎች የሕግ ከለላና ድጋፍ ሁሉ አቀፍ ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለተጎጂዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ወንጀለኞችንና ተባባሪዎቻቸውን ለህግ በማቅረብ ማህበረሰቡ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ከመድረክ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን