በክላስተር ቴክኖሎጂ በመዝራት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትጋት እየተሰራ እንደሚገኝ የከምባታ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

በክላስተር ቴክኖሎጂ በመዝራት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትጋት እየተሰራ እንደሚገኝ የከምባታ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

በዞኑ አንጋጫ ወረዳ ፋንዲዴ ቀበሌ በቱማ ክላስተር በኩታ ገጠም 110 ሄክታር ማሳ በክላስተር ቴክኖሎጂ በማልማት የዘንድሮው የመኸር እርሻ ዘር ማስጀመሪያ መርኃግብር በይፋ ተካሂዷል።

በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ፤ ጠንካራ የማሳ ዝግጅት፣ በቂ የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት በማድረግ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከምንጊዜውም የበለጠ በትጋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኩታገጠም የማሳ ዝግጅት ለክትትል፣ ለእንክብካቤ፣ ለአረም ቁጥጥርና ለተጓዳኝ ዘመናዊ የግብርና ድጋፍ ሥራዎች እና ለአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት መጨመር ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል።

የክላስተር ማሳ ዝግጅት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ማህበረሰቡ የተሻለ ኑሮ እንዲኖር ያደርጋል ያሉት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሄራሞ ናቸው።

አቶ ተሾመ አክለውም አንጋጫ ወረዳ በግብርና ዘርፍ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ቀድሞ በመዘመን በዞኑ የተሻለ አፈጻጸም እያሳየ የመጣ ወረዳ በመሆኑ ህዝቡ እና አመራሩ ተባብሮ በመስራቱ የተሻለ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመው አሁንም ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሁሉም አካባቢዎች እየተለመደ የመጣውን በክላስተር የመዝራት ቴክኖሎጂ ይበልጥ ለማጠናከር መንግስት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭትን ፍትሐዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ክትትል እያደረገ መሆኑንም አቶ ተሾመ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ከክላስተር ቴክኖሎጂ ጋር እየተላመደ ጥቅሙን ተረድቶ በፉክክር እየሰራ መሆኑን በመግለጽ በግብዓት አቅርቦት በኩል የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሆነ አቶ ተሾመ አክለዋል።

ማሳቸውን በኩታገጠም በክላስተር ቴክኖሎጂ በዘር እየሸፈኑ አግኝተን ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች በበኩላቸው፤ በወቅቱ የአረም ቁጥጥር ስራዎችን ለማከናወን በኩታገጠም መዝራት ምቹ ሁኔታን እንደምፈጥርላቸው ተናግረዋል።

አክለውም ማሳቸውን በበቂ ሁኔታ አዘጋጅተው አስፈላጊውን ግብዓት በመያዝ ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ: አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን